ሞት በጥር በነሀሴ መቃብር እነዴት ይሆናል ቢሉ?🤔
ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በቅንአት መንፈስ ተነሣሥተው
ቀድሞ ልጇን በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣል እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንም እንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን?
ኑ ተሰብሰቡና ሥጋዋን በእሳት እናቃጥላት ብለው ተማክረው መጡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን የአልጋ ሸንኮር በድፍረት ያዘ፡፡
የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ በእውነት የአምላክ እናት ናት በማለት ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደነበሩ ሆነውለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡
ቅዱስ ዮሐንስም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወደ ሐዋርያት ሲመጣ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ በ14 ቀን ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ስለሰጣቸው በታላቅ ዝማሬ፣ በውዳሴ ወስደው ቀድሞ በተዘጋጀው መካነ ዕረፍት በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡
የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት በተፈጸመ ጊዜ ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ፣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን እንደ ልጇ ትንሣኤ ተነሥታ ስታርግ ያገኛታል፡፡
ቀድሞ የልጅሽን አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራው ቅዱስ ቶማስን አጽናናችው፡፡ ሄዶም ለሐዋርያት የሆነውን ሁሉ እንዲነግራቸው አዝዛው ለምልክት ይሆነው ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡
ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወደ አሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ የእመቤታችን ነገር እነዴት ሆነ? ብሎ ቢጠይቃቸው፤ እመቤታችንን እኮ ቀበርናት ብለው ነገሩት፡፡ እርሱም ዐውቆ ምስጢሩን ደብቆ
አይደረግም ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር እንደምን ይሆናል?»
አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው፡፡ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም ብሎ የእመቤታችን መካነ መቃብር ሊያሳዩት ይዘውት ሔዱ፡፡ መቃብሩን ቢከፍቱ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አጡት፤ ደነገጡም፡፡
በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች ብሎ የሆነውን ሁሉ ተረከላቸው፡፡ ከዚያም ምልክት እንዲሆን የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ እነርሱም ማረጓን አምነው ሰበኗን ለበረከት ከተከፋፈሉ በኋላ ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሄዱ፡፡
ከተመችዎ ለጓደኞችዎ ሸር ያድርጉ !
────────── ✦ ──────────
ፖሊ ግቢ ጉባዔ
📩@polygbigubaecommentbox ለሃሳብ አስተያየትዎ
📚@polylibrary መፅሐፍትን ለማንበብ
📖@polytmhirt ለኮርስ
📷@mkpoly_gallery የፎቶ እና ቪዲዮ ማኅደር
────────── ✦ ──────────
Telegram | Instagram







