ሰባት ምርጥ ትምህርቶች ከ የአመራር ጥበብ መፅሀፍ
1, ራስህን ምራ
ስኬት አጣሁ፣ ሀብት ራቀኝ የምትለው ወዳጄ የብዙ ችግሮችህ ምንጭ ራስህን በትክክልና በአግባቡ መምራት አለመቻልህ እንደሆነ ብነግርህስ?! በእንዝላልነት አትኑር፣ በስሜቶችህ አትመራ፣ በሰዎች ሐሳብ እንደ እንስሳ አትነዳ። ጨክን፤ ራስህን ልክ እንደ ወታደር በዲሲፕሊን ምራው! ለጊዜያዊ እርካታ እጅ አትስጥ!! መሪ ነህ፣ የራስህ መሪ ነህ እንጂ ተመሪ ባሪያው አይደለህም!
2, ቤተሰብህን ምራ!
የቤተሰብህ ሰላምና ስኬት በአንተ በመሪው እጅ ነው። ለሚስትህ ምን ዓይነት ባል፥ ለልጆችህ ምን ዓይነት አባት ነህ? ቤተሰብህ ተለይቶ የሚታወቀው በሰላም፣ በፍቅር፣ በሐብት ነው ወይስ በጸብና በድህነት? አሁን ቤተሰብህ ያለበት ሁኔታ ያንተን የመምራት አቅም ያመለክታል። ቤተሰብን መምራት ሀገርን እንደ መምራት ነው፤ ምክንያቱም ቤተሰብ ሀገር ነውና!
3, ድርጅትህን ምራ!
መሪ ማለት መንገዱን የሚያውቅ፣ በሚያውቀው መንገድ የሚጓዝ፣ የተጓዘበትን ለሌሎች የሚያሳይ ነው ይባላል። ድርጅትህ የአንተ ሌላ መልክ ነው። አንተ ከወደቅክ፣ ድርጅትህ ይወድቃል። አንተ እንደ ንስር ከፍ ካልክ ድርጅትህም ከፍ ይላል። ለሰራተኞችህ እንደ አባት የሚመክር፣ እንደ እናት የሚራራ፣ እንደ ወንድም የሚጠብቅ፣ እንደ እህት የሚንከባከብ፣ እንደ ኃላፊ ሰርቶ የሚያሳይ መሪ እንጂ—
በአፉ የሚመርዝ፣ በትዕዛዙ የሚያስደነግጥ ክፉ አለቃ አትሁንባቸው። ድርጅትህን እንደ ድርጅታቸው እንዲያዩ እንጂ ለባዳ እንደሚለፉእንዲሰማቸው አታድርጋቸው።
4, አካባቢህን ምራ
አካባቢህን ምራው እንጂ በእሱ ልክ ሆነህ አትገኝለት። በሰዎች ከንቱ ሐሳብ፣ በዘልማዳዊ አስተያየት አትደንግጥ፣ አትወሰን። ሁልጊዜም በሐሳብና በስራ የሚመራ ባለራእይና ደፋር ሆነህ ተገኝ።
5, ተከታዮችህን ምራ
ተከታዮችህ ነገ እንዳንተ የሚሆኑ ልጆችህ ማለት ናቸው። ለልጆችህ ትልቅ ምሳሌ መሆን እንደሚጠበቅብህ ሁሉ፣ ለተከታዮችህም ግዴታ አለብህ። መሪነትህ እንደ ታላቅ ወንድም ይሁን። ሰርተህ አሳያቸው፤ ሲያጠፉ ምከራቸው፤ ሲናገሩ ስማቸው። ተከታዮችህን ምራ፣ ተከታዮችህን አፍራ!
6, ሀገርህን ምራ
በሀሳብ፣ በተግባር፣ በእውቀትና በጥበብ ሁሉ ሀገርህን ምራ እንጂ በሀገርህ ሁኔታ አትመራ። ፍጥነትህ በዓለም እርምጃ ልክ እንጂ ባለህበት ቦታና ሀገር ብቻ አይወሰን። ሀገር የመሪ ያለህ እያለች ነው። አንተ እንድትመራት፣ እንድታስተዳድራት፣ ታላቅ ነገርን እንድትሰጣት ትፈልጋለች።
ሀገር የምትመራህ ብቻ ሳይሆን አንተም ሀገርን የምትመራ ሁን!
7, ዘመንህን ምራ!
ዘመኑን የሚቀርጽ እንጂ ዘመኑ የሚቀርጸው አትሁን። ዘመንን የሚመሩት፣ መልክ የሚሰጡት ጥቂት መሪዎች ናቸው። አንተ ከእነዛ መሐል ለመሆን ምን ያግድሃል? ምንም አያግድህም!! ማሰብ ትችላለህ፣ መስራት ትችላለህ፣ መፍጠር ትችላለህ።
✍️