ህይወትን በጥበብ: post #1418 — TG.ME

የምትደውይ መስሎኝ
ታውቅያለሽ የኔ አለም.
ግራ ጎኔን ያጣሁ ጎዶሎ ብሆንም
የብቻ መኖርያ ጎጆ አልሰራሁም
ቤት አልተከራየሁ ጥገኛ ላጤ ነኝ
ላንቺ መስተንግዶ ሞባይሌ ነው ያለኝ.
ይህንን ነግሬሽ ደውይልኝ ስልሽ
አይሆንም አላልሽም እሺ ነበር መልስሽ
ያልሺውን አምኜ የምትደውይ መስሎኝ
በሀሴት ማእበል የምሆነው ጠፍቶኝ
ሽር ጉድ አልኩልሽ ደውልሽን ልቀበል
በሞባይሌ ታምቡር ድምጽሽ እንዲዋልል.
በስልኬ አያያዝ ሆዴ እንዳይከፋሽ
ያመቀው አቧራ እንዳያስነጥስሽ
የተቼን መስታወት እስክሪን ወልውዬ
የሽንቁሩን አፈር ቅንጣቲት አጥልዬ
ከጉሮሮሽ ጅረት ድምጽሽ ሲንፎለፎል
አድማሱን አካሎ በሞገድ ሲዋልል
ስርቅርቅ እያለ ደርሶ ሲወረወር
እንቅፋት እንዳይሆን የስልኬ እስፒከር
የሞባይሌ ጠረን ከረበሸሽ ብዬ
በአንቴናው ምትክ ሰንደሌን ተክዬ
ያንደበትሽን ለዛ ኔቶርክ እንዳይውጠው
የጆሮዬን ምግብ ቀድሞኝ እንዳይበላው
እያቆራረጠ ከኔ እንዳያስቀረው
በርቀት ተጉዤ ካለሁበት ሰፈር
ዋርካው ላይ ወጥቼ ከመንደሩ አድባር
የደውልሽን ጥሪ ስጠባበቅ ነበር.
ከዛፉ ቅርንጫፍ ብቻዬን ነበርኩኝ
ከጆሮዬ አጠገብ አንቺን እያሰብኩኝ
የሚገርምሽ ነገር!
ድምጽሽን መጠበቅ ራስ ወዳድ አድርጎኝ
ሳወራሽ ቢሰሙ የሚሻሙኝ መስሎኝ
አሞራ ወፎቹን ከዛፉ አባረርኩኝ.
የምናወጋበት ስአቱ ሲዳረስ
ልቤ ተቅለስልሶ ንግግሬ እንዳይፈርስ
ቃላትን ሰድሬ አንደበቴን ስዬ
ያልሺው እንዳያልፈኝ,
የጆሮዬን ኩክ ከውስጡ መንግዬ
የምትደውይ መስሎኝ በተስፋ ቆየሁሽ
ዛሬም እንደትላንት ቃል ማጠፍ ለምዶብሽ
ትደውያለሽ ስል ሳትደውይ ቀረሽ.
አውቃለሁ ፍቅር አለም,
ላለመደወልሽ መንስኤ ይኖራል
ሆኖም ለመቅረትሽ ምክንያት ከመኮልኮል
ቃልን ላለመስጠት ማሳበብ ይሻላል
መጣሁ ብሎ መቅረት
ፉት ብሎ እንደመትፋት እንዴት ይቀልሻል?
እንኳን ጉጉ ልቤ ስልኬም ታዝቦሻል.

በጀልፑ ተስፋዬ ለተጨማሪ ግጥሞች ቻናላችንን ይቀላቀሉ

ቻናላችንን ለመቀላቀል፦ https://t.me/litrature2018
Telegram
ብእረ ብሬል
ይህ ቻናል የተከፈተው በጀልፑ ተሥፋዬ አማካኝነት ሢሆን በዋነኛነት ሥነ/ጽሁፋዊ ዘውግ ያላቸው ኪነ/ጥበባዊ ሥራወች አሥተማሪና አዝናኝ በሆነ መልኩ በቻናሉ ባለቤት እየተዘጋጁ ይቀርባሉ. አሥፈላጊ ሢሆን ደግሞ የሌሎች ሠወች ሥነጽሁፎች ይለቀቃሉ ለአቅራቢወቹም ተገቢው እውቅና ይሠጣል. መልካም ጊዜ እንዲኖረን እመኛለሁ.
❤5👏2