የማይነጥፍ ብርሃን እልፍ ርቀቶችን ከላይ ተወርውራ፣ ጽሀይ ብትፈነጥቅ የብርሀን ጮራ፣ ሙቀት ብትቸረን ከሰማያት… — ህይወትን በጥበብ — TG.ME

የማይነጥፍ ብርሃን
እልፍ ርቀቶችን ከላይ ተወርውራ፣
ጽሀይ ብትፈነጥቅ የብርሀን ጮራ፣
ሙቀት ብትቸረን ከሰማያት ወርዳ፣
ሢመሽ አትታይም በጽልመት ተጋርዳ።
ድቅድቁን ጨለማ በሀይሏ ሠንጥቃ፣
ከዋክብት አሥከትላ ብትወጣ ጨረቃ፣
ማራኪ ፈገግታ ሀሤት ብታጭርም፣
ወፎችን አጅባ ማለዳ አትዘምርም።
አንቺ ግን እማዬ፣
ጠዋት የመለብስሽ የሙቀት ሸማዬ፣
ማታ የማበራሽ የተሥፋ ሻማዬ፣
የነፍሤ እሥትንፋሥ፣ የልቤ ትርታ፣
የመኖሬ ምክንያት፣ የህይወቴ ዋልታ፣
የአካል ጡንቻዬ፣ የመንፈሥ ብርታቴ፣
ሞያ ጥበቤ ነሽ፣ ርቱእ አንደበቴ፣
ብእር መጨበጭያ መዳፍ የሠጠሽኝ፣
በጨለማ ሆነሽ ብርሃን ያሣየሽኝ፣
ብሩህ አይምሮዬ፣ የአይን ብሌኔ፣
እናቴም አባቴም፣ ተሥፋ ወጋገኔ።
ሀቅ ነው አውቃለሁ፤
ሻማ ለወዳጁ በእሣት ይቀልጣል፣
የማ መሠዋት ግን ከመቅለጥ ይልቃል።
የሻማ ብርሃን ከሥአታት እድሜ ከቶ አይሻገርም፤
የማ ወጋገኗ በቀንና ሌሊት በጊዜ አይለካም።
❤13🥰1
July 8, 2026 960 2