የረቢዕ ስጦታ ፈንታም እጣዬ ነሁ፣
የሺ አምስት ኡመትሁ ሀበሻ ላይ ያለሁ፣
ስከትብ ስላንቱ በማውቀው በአጀሙ፣
ስልዎት አለሁኝ አንቱ ሙከረሙ።
በረቢዕ ነው እና
ጀምበር መገለጡ፣
በረቢዕ ነው እና
ከዞላም ማምለጡ፣
አናውን ዳናውን ንጉሱን ከአልከሶ፣
ዊላዳሁ ሞሸረው ቀለም አስፈስሶ።
ውልደትዎ ወልዶ
እዝነት ከደግነት፣
ዞላም ሊገረሰስ
ኑር በኑሩ ሊመረት፣
አሚና አዝልቃወት
ቀኑ ደረሰና፣
አለማት ተቸሩ
ሸረፍ ከልቅና።
ዳና የዘነበው የሸህ ሚስባሁ ቃና፣
በጫሌ ላይ ቢጎርፍ የውልደትሁ ዜና፣
በርዘንጅ የፈሰሰው በሙላው ነውና፣
ገሌ ገሌ አንልም ሰምጠን ያለ ዋና።
ይሄ ወራት እማ
እጅግ ሰው ቢያዘልቅ፣
የኪስራን ጉልላት
ፈራርሶ ሲወድቅ፣
የሺ አመት እሳቱ
ክፋቱ ሲላቀቅ፣
ደርቆ የሰዋ ሀይቅ
ኢብሊስም ሲያንቧርቅ፣
ታዬ በውልደትሁ ነቢይ በአንቱ መዝለቅ።
ከአሚና ማህፀን ኑር ፈሶ ሻም ደርሶ፣
ፅልመት ወገግ አለ ብርሀን ደግሶ፣
እኔም አንቱን ብዬ ከመስመሩ ሳርቅ፣
ሁሌ አረሳዎትም ረቢዕ ሲዘልቅ።
#በፈትሁዲን_ዑመር
1448 ዐ.ሂ





