.
.
.
---------------ትናገር
ትናገር አኢሻ
የደጉን ሰው ውበት
የደጉን ሰው እዝነት
የደጉን ሰው አህላቅ
ትናገርም ታውጋ
የፊቶን አሳሳቅ።
የግንባርዎ ኑር የአካልዎ ብርሀን፣
ዞላም ማባረሩን አኢሸቱ ታውጋን፣
መርፌ ተደብቃ ጠፍታ ወድቃ ያኔ፣
ተገኘ ትላለች ብቅ ቢሉ ዘይኔ።
ፀባዬ ቁርአን
ተራማጅ በመንገድ ፣
እንዴት ነሁ በጠና
እንዴት ነሁ ሙሀመድ።
ጫማዎን ጠግነው ታይተዋል ሙስጦፋ፣
ልብስዎን በመርፌ ሰፍተዋል በይፋ፣
ቤትዎን ሲያፀዱ ሲወጡ ሲወርዱ፣
በእጅግ መተናነስ ታዩ ሙሀመዱ።
ከአፋቸው ለአንድ ቀን መጥፎ መቼ ፈልቃ፣
በመልካም ላይ ኖሩ ሀያት እስኪያበቃ፣
እንዲህ እንዲህ ብላ ብትነግረን አኢሻ፣
ነፍሳችንን ፈተሽን ብትሆነን ወጌሻ።
ስለ ውበትዎ ደግሞ ስታወራ፣
ፈገግ ያሉ ለታ
የእኛ ኸይረል ወራ፣
እንደ ቁራጭ ቀመር
ነበረ ትላለች ፊትዎ ሲያበራ።
ደግሞ እንዲህ ትላለች አኢሻ ሚስታቸው፣
እኒያ ወይዛዝርቶች
ዩስፍን ቢያይዋቸው፤
ጣታቸውን ቆርጠው
ቢደማም እጃቸው፤
ግና የእኔን ነቢይ
በድንገት ቢያይዎት፣
ጣታቸውን ሳይሆን
ልብ ነው ሚቆርጡት።
ፅድት ያለ ውበት ልስልስ ነው ገላቸው፣
ከሚስክም በላይ ነው ነቢይ ጠረናቸው፣
ከላይ የሚያበሩት የኑሩ አውድማ፣
ውስጣቸውም ነበር የምግባሮች አርማ።
ሰለዋቱ በዝቶ ናኝቶ በአለማቱ፣
መጉደል እየራቀው ጠርቶ ከጉድለቱ፣
በአንቱ ቤተ ዘመድ ደግሞም በጓድዎ፣
የአላህ ሰላት ሰላም ሁሌ አይለይዎ።
ተፃፈ-በፈትሁዲን ዑመር
1448ዐ.ሂ/2018ዐ.ል
.
.
.
#ኢንፋቅ_ሚዲያ
#ኢንፋቅ
