#የእግዚአብሔርን_አባትነት_መረዳት (1)
እግዚአብሔር ታውቆ የማይጨረስ ቢሆንም እንደ አባት ልጆቹ ራሱን በሚገባ እንድያውቁትና እንድገነዘቡት ይፈልጋል። ምክንያቱም አባቱን ጠንቅቆ የማያውቅ ልጅ ቤቱ ኾኖ ይጠፋል፤ ቤቱ ኾኖ ተስፋ ይቆርጣል፤ ቤቱ ኾኖ ባይተዋር ይሆናል። የአባቱን አባትነት ያላመነ ልጅ በአባቱ ላይ ያምጻል። የአባቱን የአባትነት ምክሩንና ተገሳጹን ችላ ብሎ ራሱን ለጥፋት ያቀርባል። እግዚአብሔር የሁሉ ፈጣሪ ቢሆንም የሁሉም ግን አባት አይደለም። ኢየሱስ ሲናገር “እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ የአባታችሁንም ምኞት ልታደርጉ ትወዳላችሁ። እርሱ ከመጀመሪያ ነፍሰ ገዳይ ነበረ፤ እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና” (ዮሐንስ 8፥44) ብሎ ነበር። #እግዚአብሔር_አባትነቱ_በክርስቶስ_ለወለዳቸው_ልጆች_ብቻ_ነው። “ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው” (ዮሐንስ 3፥3)።
የአባቱን ማንነት በሚገባ ሳያውቅ በቤቱ የምኖር ልጅ ከባሪያ አይሻልም። የእግዚአብሔርን አባትነት በሚገባ አለማወቅ ከደረጃ በታች ያኖራል።
#ልጅነት_በእግዚአብሔር_ላይ_የጥገኝነት_ሕይወት_ነው።
አባት (Father) የምለው ቃል በግሪኩ Patēr (Pat-ayr') የሚል ሲሆን፤ ጠለቅ ብለን ስናጠና የተለያዩ ትርጉሞች አሉት።
#የመጀመሪያው_ትርጉም፤ መጋቢ (Nourisher) ማለት ነው። ልጅ እግዚአብሔርን አባቴ ነው ስል፤ እግዚአብሔር መጋቢዬ ነው ማለቱ ነው። አባቱ የሚመግበው ልጅ ከሁለንተናዊ ጤንነት ጋር ከሩቅ ያስታውቃል። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ "የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምንም ሁልጊዜ ከቶ አይጠማም” (ዮሐንስ 6፥35)።
“ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፥ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” (ማቴዎስ 6፥26)
#ሁለተኛው_ትርጉም፤ ጠባቂ (Protector) ማለት ነው።
ልጅ እግዚአብሔርን አባቴ ነው ስል፤ እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው ማለቱ ነው። አባቱ ጠባቂው የኾነለት ልጅ ያለ ነውጥ ይኖራል። መጽሐፍ ሲናገር "እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም። እነሆ፥ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም። እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፥ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል። ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት። እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል። ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘላለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል" (መዝሙር 121:3-8) ይላል።
"አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም" (ኢሳይያስ 43:1-2)።
#ሦስተኛው_ትርጉም፤ ደጋፊ (Upholder) ማለት ነው።
ልጅ እግዚአብሔርን አባቴ ነው ስል፤ እግዚአብሔር ደጋፊዬ ነው ማለቱ ነው። አባቱ ደጋፊው የኾነለት ልጅ ጸንቶ ይኖራል። መጽሐፍ ሲናገር “የኃጥአን ክንድ ትሰበራለችና፤ እግዚአብሔር ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል” (መዝሙር 37፥17)።
#አራተኛው_ትርጉም፤ አመንጪ (Generator) ማለት ነው። ልጅ እግዚአብሔርን አባቴ ነው ስል፤ እግዚአብሔር መገኛዬ (አመንጪዬ) ነው ከእግዚአብሔር ወጥቻለሁ ማለቱ ነው። አባቱ መገኛው የኾነለት ልጅ በልጅነት ስልጣን በመግዛትና በማስተዳደር ሕይወት ይኖራል። ወራሽነቱም የተረጋገጠ ነው። ምንጭ ይሆናል። ኢየሱስ ለሳምራዊቷ ሲናገር “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ አላት” (ዮሐንስ 4፥14)።
#አምስተኛው_ትርጉም፤ የቤተሰብ መስራች (Originator of a Family) ማለት ነው። ልጅ እግዚአብሔርን አባቴ ነው ስል፤ እግዚአብሔር የቤተሰቤ መስራች ነው ማለቱ ነው። አባቱ የቤተሰቡ መስራች እንደኾነ የተረዳ ልጅ በቤተሰቡ አያፍርም፤ ከምንም ምክንያት ተነስቶ አሁን የምኖርበትን ቤተሰቡን አያሳፍርም። “አባትህንና እናትህን አክብር፤ እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ዕድሜህ እንዲረዝም” (ዘጸአት 20፥12)