#ታቦርን_ተመኘሁ
"የሚትለውን አታውቅም" ትሉኝ ይሆናል። እኔ ግን፦
✍️ ከሥራቸው ይልቅ ክብራቸው በሰዎች ዘንድ ለማጉላት በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ራሳቸው ከሚደሰኩሩ፣ ያለ ይሉኛታና ያለ ሃፍረት ከግብራቸው በላይ ራሳቸውን ከቆለሉ፣ መልካም ሥራ ባይኖራቸውም በሌላው ሓጢአት ላይ ለመፍረድ በፍርድ ወንበር ራሳቸውን ከሰየሙ፣ ከእነዚህ ራቅ ብሎ በታቦር መሆን ተመኘሁ።ማቴ 6፡2-5፣ ማቴ 7፡1-2
✍️ መልካሙን ታሪካችን ጥላሸት እየቀቡ፣ ባለውለታቸውን እየካዱ፤ በራሳቸው ላይ የባእዳን ትርክትን እየጫኑ፤ እንደ እርያ ወርቅ የማያምርባቸው፤ የታሪካቸው ምሰሶ የሚነቅሉ፣ ከትቢያ ይነሱ ዘንድ ትቢያ ልሳ መግባ - በሰዎች የክብር መጠን ይኖሩ ዘንድ ከባርነት ጠብቃ ያሳደገቻቸውን ተመልሰው ከሚረግጡ (ከሚነክሱ)፣ የሚያገለግሉትን ሕዝብ በቃል ብቻ እያታለሉና እየዋሹት ከሚኖሩ ተለይቶ በታቦር መኖር እንዴት አያስመኝ? ማቴ 7፡6-21
✍️ መልካም የሠራ ከሚከሰስበት፣ መልካም ከማድረግ ይልቅ መልካም የሚያደርገውን ለመክሰስ እቅድ ከሚያዝበት "ጻፎችና ፈሪሳውያንም መክሰሻ ሊያገኙበት በሰንበት ይፈውስ እንደ ሆነ ይጠባበቁት ነበር" እንደተባለ። ሉቃ 6፡7፣ ለሌላው በተደረገለት መልካም ነገር በቅናት ከሚቃጠሉበት፣ በተአምር (ምልክት) ካልሆነ እምነት ከጠፋበት፣ በሐሰትና በፖለቲካ ጥላቻ ሰክሮ የሰውን አካል እየቆራረጠ ስጦታ ከሚሰጣጥ (ሄሮድሳዊ) በዚህ ህዝብ መካከል ከመኖር፣ ወገኔን በማጭበርበርና በሌላው ላብ ከሠራሁት የሞቀና የተደላደለ ቤት ያለ ዳስም ቢሆን በታቦር መኖር ይሻለኛልና ይሄንን ተመኘሁ። ማቴ 12-14
✍️ ደግሞም የባሰውን ላለማየት የሕዝቤ ሌላ ክስ፣ ሌላ መከራና ስደት፣ መታረድ ለቅሶና ዋይታ ከምመለከት እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በታቦር መኖርን አስመኘኝ።
✍️ በስስት ከተሸበበው፣ ሁሉ ለእኔ ብቻ ከሚለው፣ በእኔ ለእኔ የሚለውን ለማግኘት በሌላው ላይ በሚረማመደው መሃል ከመኖር፤ የአንተ ክብር በሚገለጥበት፣ አንተ ያከበርካችውን ቃል ብቻ በሚደመጥበት በተቀደሰው ተራራ (2ኛ ጴጥ 1፡17-18 )መኖር።
አንተ ደግሞ ማን ሆነህ ነው? ለራስህ ከዚህ ውጹእ ነህን? ከፍጹማኑ ጋር ለመኖር መመኘት ብቻ በቂ ነውን? ትለኝ ይሆናል። ካንተ/ቺ የባስኩ ደካማ ቢሆን እንጂ ከደብረ ታቦር በፊት “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ (ማቴ 16፡24)” ያለውን ቃል ማሰብ ይቀድማል። #መስቀሉን መሸከም ቢያቅተኝ ሰብብ ፈለግኩ እንጂ።
ትንሣኤው ደግሞ ከመከራ በኋላ ነው። ወንጌላዊው ሉቃስ ቅዱስ ጴጥሮስን “የሚለውንም አያውቅም ነበር (ሉቃ 9፡33)” ያለው ለዚህም አልነበር!
12/12/12
መቐለ ተጻፈ
1August 18, 2026 79