ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለ #መንፈሳዊ_ጉዞዎች - የቀጠለ "ታዲያ በውስጡ [በጉዞ] ያለው ጎጂ ነገር ምንድን… — Gebreab Hagos (ዘ-አብ) — TG.ME

ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለ #መንፈሳዊ_ጉዞዎች - የቀጠለ

"ታዲያ በውስጡ [በጉዞ] ያለው ጎጂ ነገር ምንድን ነው? ቅዱስ ሕይወት ለሁሉም ማለትም ለወንዶችም ለሴቶችም እኩል ነው። የዝያ የመንፈሳዊ ተዐቅቦ (ኮንተምፕሌቲቭ) ሕይወት ልዩ ምልክት ተዐቅቦ ነው። ነገር ግን ተዐቅቦ የሚጠበቀው በሥርዓት ሲኖሩ ነው። ስለዚህም ከተቃራኒ ጾታ ጋር መገናኘትና መደባለቅ መኖር የለበትም። ወንዶች ከሴቶች ጋር ወይም ሴቶች ከወንዶች ጋር ሆነው የተዐቅቦን ሕጎች መጠበቅ አይቻላቸውም።
ነገር ግን የጉዞዎቹ አስገዳጅ ሁኔታዎች ይህንን መንፈሳዊ ጥንቃቄ ሁልጊዜ ወደ ልቅነትና ወደ ግድ የለሽነት ደረጃ ዝቅ ለማድረግ የተዘጋጁ ናቸው።

የምሥራቁ ዓለም ማደሪያዎች (እንግዳ ማረፊያዎች)፣ ሆቴሎችና ከተሞች ደግሞ የልቅነትና ለኃጢአት ግድ የለሽ የመሆን በርካታ ምሳሌዎችን የሚያሳዩ እንደመሆናቸው መጠን በዚያ ሁሉ ጢስ ውስጥ የሚያልፍ ሰው ዓይኖቹ ሳይቃጠሉ ማመልጥ እንዴት ይቻለዋል? ጆሮና ዓይን እንዲሁም ልብ እነዚህን ሁሉ እጅግ ክፉ ነገሮች በዓይንና በጆሮ በመቀበል በሚረክሱበት ቦታ፤ እንዲህ ካለው ተላላፊ የበሽታ ማዕበል ሳይበከሉ ማለፍ እንዴት ይቻላል?

ደግሞስ በኢየሩሳሌምስ አዲስ የምናገኘው ነገር ምንድን ነው? "በዚያ የተገለጠው ክርስቶስ እውነተኛ አምላክ መሆኑን እንረዳለን፤ ነገር ግን ወደ ኢየሩሳሌም ከመምጣታችን በፊትም ይህን ታምነን ነበር፣ ከጉዞአችን በኋላም እምነታችን አልቀነሰም ወይም አልጨመረም። ወደ ቤተልሔም ከመምጣታችን በፊት እርሱ ድንግል ማርያም በሥጋ ሰው መሆኑን እናውቅ ነበር። መቃብሩን ከመየታችን በፊት በሙታን ትንሣኤ እናምን ነበር። የደብረ ዘይት ተራራን ከመየታችን በፊት የእርሱን ወደ ሰማይ ማረግ እውነተኝነት ታምነን ነበር። ከቀጰዶቅያ ወደ ፍልስጤም ከሚደረግ ጉዞ ይልቅ 'ከሥጋችን ተለይተን ወደ ጌታችን መጓዝ' የበለጠ አስፈላጊ ነው።

የእግዚአብሔርን ህልውና በሚታዩ ምልክቶች ብቻ መቀበል የሚቻል ቢሆን ኖሮ ከእነዚያ ቦታዎች [ከኢየሩሳሌም] ይልቅ እርሱ በቆጶዶቅያያ (Cappadocian) ሕዝብ ዘንድ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይበልጥ ተገቢ በሆነ ነበር። ምክንያቱም የጌታችን ስም የሚከብርባቸው ስንት መሠዊያዎች በዚያ አሉ! በሌላው ዓለም ሁሉ ያሉትን ያህል ለመቁጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው።

ደግሞም መለኮታዊ ፀጋ ከሌሎች ቦታዎች ይልቅ በኢየሩሳሌም አካባቢ በሙላት የሚገኝ ቢሆን ኖሮ በዚያ በሚኖሩት ዘንድ ኃጢአት እንዲህ የተለመደ ባልሆነ ነበር። ነገር ግን እንደምናየው በእነርሱ ዘንድ ያልተፈጸመ ምንም ዓይነት የርኩሰት ዓይነት የለም። አታላይነት፣ ዘሙት፣ ስርቆት፣ ጣዖት ማምለክ፣ መርዝ መስጠት፣ ጭቅጭቅና ግድያ በዙሪያው የሞሉ ናቸው። ግድያ ደግሞ እጅግ የበዛ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎች ሌለውን ለመዝረፍ ሲሉ ብቻ እንደ የዱር አራዊት እርስ በእርሳቸው በሚጠቃቁበትና የወንድሞቻቸውን ደም በሚያፈሱበት በዚያ ስፍራ እንዳለው ያህል እርስ በእርስ ለመገዳደል የተዘጋጀ ሕዝብ በዓለም ላይ የለም። ታዲያ እንዲህ ያሉ ነገሮች በሚፈጸሙበት ቦታ የመለኮታዊ ፀጋ ሙላት እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለህ ብዬ እጠይቅሃለሁ?

ነገር ግን ከተናገርኩት ሁሉ በኋላ ብዙዎች የሚሰጡትን መልስ አውቃለሁ። እነርሱም፦ «ይህንን ሕግ ለምን ለራስህ አልደነገግህም? እዚያ የሄደ ተጓዥ በመጓዙ የሚያገኘው ጥቅም ከሌለ ለምን የዚያን ያህል ረጅም መንገድ ደከምህ?» ይሉ ይሆናል። ለዚህ ያለኝን ምላሽ በእኔ ዘንድ ይስሙ። አንደኛ ፦ ሕይወቴን በሰጠኝ ጌታ በተሾምኩበት የአገልግሎት ኃላፊነት አስገዳጅነት ቅዱስ ሲኖዶሱ የወሰነውን ውሳኔ ተቀብየ በዓረቢያ ያለችው ቤተ ክርስቲያን የምትገኝባቸውን ቦታዎች መጎብኘት ግዴታዬ ነበረ። ሁለተኛም፦ ዓረቢያ ከኢየሩሳሌም ክልል ወሰን አጠገብ በመሆኗ በኢየሩሳሌም ባሉ ቅዱሳት አብያተ ክርስቲያናት አባቶች ዘንድ ነገሮች በመበላሸታቸው አስታራቂ ይፈልጉ ስለነበር ከእነርሱ ጋርም ለመነጋገር ቃል ገብቼ ነበር። ሦስተኛም፦ እጅግ ሃይማኖተኛ የሆነው አውጉስቶሳችን (ንጉሠ ነገሥቱ) በመልእክት ማጓጓዣ (ፖስታ) የመጓዝ ዕድል ስለሰጠን በሌሎች ዘንድ ያየናቸውን ተስፋ አስቆራጭና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ አልተገደድንም።

ይልቁንም ምክራችን በዓይኖቻችን ባየናቸው ነገሮች ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ይበልጥ ሊደመጥ ይገባዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ በኢየሩሳሌም ከመቆየታችን በፊትም ሆነ በኋላ እናምናለን። በእርሱ ላይ ያለን እምነት ከዚያ በኋላ አልጨመረም ወይም ደግሞ አልቀነሰም። ቤተልሔምን ሳናይ በፊት ከድንግል ሰው መሆኑን እናውቅ ነበር፤ መቃብሩን ሳናይ በፊት ከሙታን ተለይቶ መነሣቱን እናምን ነበር፤ የደብረ ዘይት ተራራን ሳናይ ወደ ሰማይ ማረጉ እውነተኛ እንደሆነ እንመሰክር ነበር። ወደዚያ ከመጓዛችን ያገኘነው ጥቅም ቢኖር የራሳችንን ቦታዎች እዝያ ካሉት ጋር በማወዳደር የእኛ ቦታዎች እጅግ ቅዱሳን መሆናቸውን ማወቃችን ብቻ ነው።

ስለዚህ እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ! አሁን ባላችሁበት ቦታ ሁሉ አምላክን አመስግኑ። የቦታ መለዋወጥ ወደ እግዚአብሔር መቅረብን አያመጣም። የአካልህ ክፍሎች እርሱ በአንተ ዘንድ ሊኖርና ሊመላለስባቸው የሚችሉ ሆነው ከተገኙ እግዚአብሔር ወደ አንተ ይመጣል። ነገር ግን የውስጥ ሰብእናህን በክፉ አሳቦች የተሞላ ከሆነ በጎልጎታ ብትሆን፣ በደብረ ዘይት ተራራ ብትሆን፣ ወይም በትንሣኤው መታሰቢያ ድንጋይ ላይ ብትቆም እንኳ ክርስቶስን ወደ ራስህ ከመቀበል ይልቅ ገና እርሱን ማመን እንኳ እንዳልጀመረ ሰው እጅግ የራቅህ ትሆናለህ።

ስለዚህ ወዳጄ ሆይ! ወንድሞች ከቆጶዶቅያ ወጥተው ወደ ፍልስጥኤም ከመሄድ ይልቅ ከሥጋ [ሥጋዊ ፍላጎት] ተለይተው ወደ ጌታችን እንዲሄዱ ምከራቸው። ማንም ሰው ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ የተናገረውን ትእዛዝ እንደ ማስረጃ ቢያቀርብ እውነተኛ ትርጉሙን እንዲረዳ አድርገው። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታና በመንፈስ ቅዱስ መሞላት ገና በሐዋርያት ላይ ስላልወረደ ጌታችን ከላይ ኃይል እስኪለብሱ ድረስ ባሉበት ቦታ እንዲቆዩ አዟቸዋል። አሁን ግን በመጀመሪያ ደረጃ መንፈስ ቅዱስ እያንዳንዱን ስጦታ በነበልባል መልክ ሲወርድ የነበረው ነገር እስከ አሁን ድረስ የሚቀጥል ቢሆን ኖሮ ያ በተፈጸመበት ቦታ ሁሉም ሊቆዩ በተገባ ነበር። ነገር ግን መንፈስ «ወደሚወደው የሚነፍስ» ከሆነ ያመኑትም ሁሉ የዚያ ስጦታ ተካፋይ ይሆናሉ። ይህም በእምነታቸው መጠን እንጂ ወደ ኢየሩሳሌም በሚያደርጉት ጉዞ ምክንያት አይደለም።"
August 29, 2026 42