፡
ስለማላጎድል
ሁሉም ነገር ቦታ ቦታውን ይዟል፡፡
አልጋ ስር ሳይቀር ቤቱን ብጥር አድርጌ አፅድቻለሁ፡፡
የቶሸሸውን እቃ ሰብስቤ አጥቤያለሁ፡፡
አልጋዬን በስርዓቱ አነጥፌአለሁ፡፡
ልብስና ጫማዎቼን ለነድያን ለመስጠት እንዲያመች አድርጌ በኩርቱ ፌስታሎች አሰናድቼ በሩ ስር አስቀምጫለሁ፡፡
ሦስት ሳምንት ሙሉ ችላ ብዬ የከረምኩትን ውሃ እያንጠባጠበ የሰነበተ የሽንት ቤቱን የእጅ መታጠቢያ ቧንቧ እንኳን ባለሙያ ጠርቼ አሠርቻለሁ፡፡
ሁሉም ነገር ቦታ ቦታውን ይዟል፡፡
ሕይወቴን ሙሉ እናንተ ቤተሰቦቼ ላይ ሸክም ሆኜ መኖሬ ሳያንስ አሁን ደግሞ የቆሸሸና የተዝረከረከ ነገር ትቼላችሁ መሄድ አልፈለግኩም፡፡
ስንት ዘመን ሙሉ ቆሻሻዬን ስታጸዱ፡ ገመናዬን ስትሸፍኑ የኖራችሁት ይበቃችኋል፡፡
አስክሬኔን መስኮት አጠገብ ያለው ሶፋዬ ላይ ታገኙታላችሁ፡፡ ብዙ ክኒኖች ወስጄ ለመሞት የመረጥኩት ፡ በጽዳት የቆየሁበትን ቤት ላለማቆሸሽ ነው፡፡በተለይ ግን መከረኛዋ ተመላላሽ ሠራተኛዬ ጌጤ፡ ጠዋት መጥታ በሩን ከፍታ ስትገባ በደም ተዘፍቄ፡ ወይ ተንጠልጥዬ አይታኝ በድንጋጤ ክልትው እንዳትል ነው፡ አምስት አመት ሙሉ አንዴ ሰው፡ አንዴ አፈር እየሆንኩ ያሰቃየኋት ይበቃታል፡፡
ዐውቃለሁ፡ ነገ ጠዋት እኔ ባልኖርም ጀምበር በሰዓቷ ትወጣለች፡፡ ሕይወትም ምንም እንዳልተፈጠረ፡ አንድም ሰው እንዳልጎደለ ዑደቷን ትቀጥላለች፡፡
ለዚህ ነው ልሄድ የወሰንኩት፡ በመሞቴ ምንም ስላማላጎድል፡ የትም ስለማልጎድል፡ ማንንም ስለማላጎድል፡፡
(ዥዋ ዥዌ)
@getmtg
@getmtg
4March 9, 2026 930