ሦስቱ ጠቢባን
ልጄ ሆይ እነርሱ ይጠብቁህ ዘንድ፤ ሕግጋትን ጠብቅ፡፡ ልጄ ሆይ በኃያላንና በጠቢባን ዘንድ ክብር ይሆንልህ ዘንድ በወጣትነት ዘመንህ ታገሥ፡፡ ልጄ ሆይ ሞገስን ይሆንህ ዘንድ የሰማኸውን ነገር ጠብቅ፡፡ ልጄ ሆይ መንፈሳዊ አባትህን ጠይቀው፡፡ እርሱም ጽድቅንና እውነትን ይነግርሃል።
ልጄ ሆይ በተሾምክበት ወራት ለድኾች ፍርድ አታጉድል፤ ሰውን ባለጸጋ ነው ብለህ አትፍራው ለዘመዶችህም ፍርድ አታድላ፡፡ ለባለጸጎችም ቢሆን የሰው ሀብቱ ንብረቱ መብዛቱ እያስፈራህ፡፡ እሰከ ዕለተ ሞትህ ድረስ እውነትን ተናገር ጠቢብ ሲራክ እንዲህ አለ፦ ለሰነፍ ራስህን ዝቅ አታድርግ፡፡ እንደ ሀብቱ ብዛት ኃጢአቱም ብዙ ነው፤ በንግግሩ ብዛት ሐሰቱ ይበዛልና፡፡
ከእግዚአብሔር እንዳትለይ ድኻውን አትግፋው፡፡ ሦስት ጠበብቶች አሉ፥ አንዱ እንደተቻለው የሚተው የሚታገሥ ነገር ኃላፊ ልበ ሰፊ ነው፡፡ ሁለተኛው እያወቀ ዝም የሚል ሦስተኛው ጠቢብ ሲሆን የዋህ ነው፡፡ ልጄ ሆይ ቸኩለህ አትናገር። ነቢይ "ቀባጣሪ አንደበት ሞትን ትጠራለች" ብሏልና፡፡ ወንድሜ ሆይ በአንደበትህ በነገር እንዳትሰናከል ተጠንቀቅ፡፡ በአንደበትህ ከምትወድቅ ወደ ገደል ብትወድቅ ይሻልሃልና፡፡ ቀባጣሪ አንደበት ብዙዎችን አወከቻቸው ከትዳራቸውም ለየቻቸው፡፡ ብዙዎችም ከቤታቸው ወጡ፤ ከሀገራቸው ተሰደዱ ከክብራቸው አነሱ፡፡
(አባ ገብረ ኪዳን - መጽሐፈ ወግሪስ ገጽ 86-84)
163
33
2
2August 26, 2026 9.5K 105