ኦርቶዶክሳውያን_ለቅዱሳን_ለምን_ይዘምራሉ? በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ክፍል ፪ ንጉሥ ዳዊት ሕይወት ላላቸው ሰዎች… — ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ — TG.ME

#ኦርቶዶክሳውያን_ለቅዱሳን_ለምን_ይዘምራሉ?
በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ክፍል ፪

ንጉሥ ዳዊት ሕይወት ላላቸው ሰዎች ብቻ ዘምሮ አላቆመም ፤ ለማትናገረውና ከእንጨት ከድንጋይ በሰው እጅ ለተሠራችው ከተማው ለጽዮን የእግዚአብሔር ማደሪያ በመሆንዋ ዝማሬን አዝንሞላታል፡፡
‹‹እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታል ፤ ማደሪያው ትሆነው ዘንድ ወድዷታል፡፡ እንዲህ ሲል ይህች ለዘላለም ማረፊያዬ ናት ፣ መርጫታለሁና በእርስዋ አድራለሁ››
‹‹እግዚአብሔር የጽዮንን ደጆች ይወድዳቸዋል ፤ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የከበረ ነገር ይባላል››
‹‹በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን ፤ ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን ፤ የማረኩን በዚያ የዝማሬን ቃል ፈለጉብን ፤ የእግዚአብሔርን ዝማሬ እንዴት በባዕድ ምድር እንዘምራለን? ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ፤     ባላስብሽ ምላሴ ከጉሮሮዬ ጋር ይጣበቅ ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ›› ብሎ ስለ ቅድስቲቱ ከተማ ሲዘምር አገኘሁት፡፡ ከራሱ አልፎም በዙሪያው ላሉት በመዝሙሩ እንዲህ ሲል ጥሪ አቀረበ     ‹‹ጽዮንን ክበቧት በዙሪያዋም ተመላለሱ ፤ ግንቦችዋን ቁጠሩ ፤ በብርታትዋ ልባችሁን አኑሩ ፤ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ›› የእግዚአብሔር ከተማ ጽዮንን ለማይወድዱ ደግሞ በመዝሙሩ ‹‹ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ ወደ ኋላቸውም ይመለሱ›› ብሎ ዘምሮአል፡፡

ዳዊት ስንት ኃጢአተኛ ሲራኮት ለሚውልና ለሚያድርባት ከተማ የእግዚአብሔር ማደሪያው እንድትሆን እንደ መረጣት አውቆ እንዲህ ሲዘምር ማየቴ ‹መንፈስ ቅዱስ ይጸልልሻል የልዑል ኃይልም ያድርብሻል› ለተባለችዋ ቅድስት ድንግል ማርያም ‹የጌታዬ እናት ፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ፣ የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ› ብዬ ለመዘመር እንድችል ኃይል የሚሠጥ ሆነልኝ፡፡ ባቢሎን በተባለ በኃጢአት ሥፍራ ሆኜ ድንግልን ባሰብኳት ጊዜ እንዳለቅስና ‹‹ድንግል ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽም ምላሴ ከጉሮሮዬ ይጣበቅ›› ብዬ እንድዘምርላት ድፍረት ሠጠኝ፡፡

የዳዊት ሲደንቀኝ ልጁ ሰሎሞን ደግሞ ‹ከመዝሙራት ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር› (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን) በተባለ ውብ ድርሰቱ ከአባቱ የባሰ የመዝሙር ቅኔን ሲቀኝ አገኘሁት፡፡ በዚህ ዝማሬው ላይ በፍቅረኛሞች መካከል የሚደረግን የፍቅር ቃል ልውውጥ ሰበብ አድርጎ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ሙሽራው ስላደረጋትና እርስዋም ‹ውዴ› ብላ ስለምትጠራው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውብ ስንኞችን ጽፎ አገኘሁት፡፡

በዚህ ዝማሬው ላይ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውድዋ የሆነውንና ነፍስዋ የወደደችውን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስን ስትፈልገው ፣ በከተማ የሚጠብቁ ጠባቂዎች የተባሉ መላእክትን ስትጠይቅ ፣ ቤተ ክርስቲያን በቀዳም ስዑር የምትዘምረው ‹እርሱ እስኪፈልግ ድረስ ፍቅርን እንዳታስነሡት› ብላ አልጋ በተባለ መቃብር ስለ ሰው ልጅ ፍቅር የተኛውን ክርስቶስን እርሱ ወድዶ ሞትን ድል አድርጎ እስከሚነሣ በእምነት እንዲጠብቁ ስትናገር ፣ ውዴ ወደ ገነቱ ወረደ ብላ ነፍሳትን ይዞ ወደ ገነት ስለ መውጣቱ ስትዘምር በሰሎሞን ዝማሬ ውስጥ አገኘሁ፡፡ በዚህ ዝማሬ ላይ ሙሽራው ስለ ሙሽራዪቱ ቤተ ክርስቲያን ቅድስናና ውበት ፣ ጡቶችዋ ስለተባሉ የቃሉ ወተት ስለሚፈስስባቸው ብሉይና ሐዲስ ኪዳን ማማር ፣ ድንቅ ቅኔ ሲዘምር አገኘሁት፡፡

በሰሎሞን መዝሙር ላይ ‹ወዳጄ ሆይ ነይ ውበቴ ሆይ ተነሽ› ‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም› የሚሉት ውብ ዝማሬዎች ለፍጡር እንጂ ለፈጣሪ የቀረቡ ምስጋናዎች አይደሉም፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ውብ ዝማሬ ሁለተናዋ በቅድስና ለተዋበችው ድንግል ማርያም መዝሙር አድርጋ የምትዘምረው፡፡ አባቱ ዳዊት ‹ልጄ ሆይ ስሚ እዪም ጆሮሽን አዘንብዪ› ብሎ ለጠራት ድንግል ልጁ ሰሎሞን ‹እኅቴ ሙሽራ ሆይ› ብሎ መዘመሩን የምንቀበለውም ከዚህ ተነሥተን ነው፡፡

ይቀጥላል.....
❤61🙏12💯6🕊1😍1
August 31, 2026 3.4K 39