#ኦርቶዶክሳውያን_ለቅዱሳን_ለምን_ይዘምራሉ?
በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ክፍል ፫
ቅዱሳንን ማመስገን በዳዊትና በሰሎሞን አላበቃም ፤ መላእክትም ለቅዱሳን ሲዘምሩ ታይተዋል፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ‹ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ደስ ይበልሽ አንቺ ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ› ብሎ ለድንግል ማርያም ያቀረበው ሰላምታ ‹ከእንዴት ውለሻል› ሰላምታ ያለፈ ምስጋና አይደለምን? ለዘካርያስ ‹አንተ ከካህናት ተለይተህ የተባረክህ ነህ› ያላለው ይህ መልአክ ለድንግል ለይቶ ያቀረበው በእርግጥም ምስጋና ነበር፡፡ ስለሆነም የገብርኤልን ሰላምታ ተውሰን ድንግሊቱን ለዘወትር እናመሰግናታለን፡፡ ገብርኤል ያቀረበውን እኛ ማቅረብ አያስፈልገንም የሚሉ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ ሆኖም ድንግሊቱ ‹ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል› ብላ መናገርዋ ለማመስገናችን ምክንያት ነው፡፡ ‹ትውልድ ሁሉ› አለች እንጂ ሰው ሁሉ አላለችምና ከየትውልዱ የማያመሰግኗት ቢገኙ አይደንቅም ፤ ከእኛ የሚጠበቅብን እንደ ኖህ ‹በትውልዳችን ጻድቅ› ሆኖ መገኘት ብቻ ነው፡፡ መልአኩ ገብርኤል ‹ደስ ይበልሽ› ቢላትም እኛ ‹ደስ ይበልሽ› አንላትም የሚሉ ሰዎች መላእክት ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ› የሚሉትን እግዚአብሔርም ‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ› ለማለት እንዴት ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ?
ለቅዱሳን የሚቀርበው ምስጋና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ያለው መሆኑን የምንደመድመው መድኃኔዓለም ክርስቶስ ራሱ ለመጥምቁ ዮሐንስ የተናገረው ምስጋና ነው፡፡ ‹‹ምን ልታዩ ወጣችሁ? ነቢይን? አዎን እላችኋለሁ ከነቢይም የሚበልጠውን … እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ማንም የለም›› (ሉቃ. 7፡26-28) ከዚህ በላይ ምስጋና ከየት ይመጣል? በዜማ መሆኑ ከሆነ ችግሩ በንባብ እንለዋለን።
የመጥምቁ ምስጋና በቅዱስ ገብርኤልም አንደበት ተነግሮ ነበር፡፡ ቅዱስ ገብርኤል የዮሐንስን ልደት ሲገልጥ ‹‹በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል›› ብሎ ነበር ፤ ወደ መዝሙር ሲለወጥ ‹ዮም ፍስሓ ኮነ በእንተ ልደቱ ለዮሐንስ› እንደማለት ነው፡፡
አባቱ ዘካርያስ ደግሞ ‹‹አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ›› ብሎ ነበር ይህም ‹ወአንተኒ ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ ፤ አርኩ ለመርአዊ ትሰመይ›› የሚለው መዝሙር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ለቅዱሳን ስትዘምር ቃላትና ግጥም የምትዋሰው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡
‹‹ሐውፅ እምሰማይ ተክለ ሃይማኖት ፀሐይ›› (ፀሐይ ተክለ ሃይማኖት ሆይ ከሰማይ ሆነህ ጎብኝ)
የሚል መዝሙር ቢዘመር ‹‹ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ›› የሚለውን የተስፋ ቃል ይዞ ነው፡፡ (ማቴ. ፲፫፥፵፫)
‹‹ጊዮርጊስ ኃያል ኮከበ ክብር›› ተብሎ ቢዘመር ‹‹ብዙዎችን ወደ ጽድቅ የሚመልሱ እንደ ከዋክብት ለዘላለም ይደምቃሉ›› የሚለውን ይዞ ነው፡፡ (ዳን. 12፡3)
‹‹አቡነ አረጋዊ ሆይ ነፍሴ ዛሬ በአንተ ፊት የከበረች ትሁን!›› ‹‹ትክበር ነፍስየ በቅድሜከ ዮም ፤ ወባርከኒ አባ አረጋዊ›› ተብሎ ሲዘመር ብንሰማ አንድ የመቶ አለቃ በነቢዩ ኤልያስ ፊት ተንበርክኮ ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ነፍሴ አሁን በፊትህ የከበረች ትሁን›› ብሎ ካቀረበው ልመና ተወስዶ ነው፡፡ (2ነገሥ. 1፡13)
በአንዳንድ ሥፍራ ለቅዱሳን በሚቀርቡ ምስጋናዎች ላይ ለፈጣሪ የቀረቡ የምስጋና ቃላት ተወስደው ለቅዱሳን ሲቀርቡ ይታያል፡፡ ይህንን የሚያዩ ሰዎች ቅዱሳን የተመለኩ ፣ የፈጣሪ የባሕርይ ክብሩ ለቅዱሳን የተሠጠ መስሏቸው ይተቻሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ለቅዱሳን በሚዘመሩ መዝሙራት ሁሉ ላይ የሚታረም ነገር አያጡም፡፡ ሆኖም ይህንን ዓይነት እርማት ላድርግ ብሎ የሚነሣ ሰው መጽሐፍ ቅዱስንም ማረም ሊኖርበት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ለእግዚአብሔር የተነገረን ቃል ለቅዱሳን ሲሠጥ በተደጋጋሚ እናገኘዋለን፡፡
ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት ፡-
‹‹ገብረ መንፈስ ቅዱስ የዓለም ብርሃን ናቸው›› ሲባል ‹‹የዓለም ብርሃን ክርስቶስ ብቻ ነው›› ብሎ የሚቃወም ቢኖር ራሱ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ ‹‹እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ ፤ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ›› ብሏል፡፡ የእርሱ ብርሃንነት የባሕርይው የቅዱሳን ብርሃንነት ግን ከእርሱ የተሠጠ ነው ብለን እንከፍለዋለን እንጂ የቅዱሳንን ብርሃንነት አንክድም፡፡ (ማቴ. 5፡14)
አንዳንድ ምእመናን ስለ ድንግል ማርያም አማላጅነት ሲመሰክሩ ‹‹ለእመቤቴ የሚሳናት ነገር የለም›› ሲሉ የሚሰማ ሰው ራሱን እየነቀነቀ ‹የእኛ ሰው Bible ላይ ብዙ ይቀረዋል› ብሎ ሊመጻደቅ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያውቅ ከሆነ ግን ‹‹እምነት ቢኖራችሁ የሚሳናችሁ ነገር የለም›› የሚለውን የጌታ ቃል ፣ ‹‹ኃይልን በሚሠጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ›› የሚለውን የጳውሎስ ቃል በሰማበት ጆሮው ‹ያመነችው ብፅዕት› ‹የልዑል ኃይል ያደረባት› ድንግል ‹የሚሳናት የለም ሲባል ከመቆጣት ይልቅ ለምእመናን የተሠጠውን እምነትና ማስተዋል ያደንቃል፡፡ (ማቴ. 17፡20 ፣ ፊል. 4፡13 ፣ ሉቃ.1፡35፣45)
ለእግዚአብሔር የተነገሩ ቃላት ለቅዱሳን ተደግመው ብናገኛቸው እንኳን ትርጉሙን እንረዳለን እንጂ የእግዚአብሔርን ክብር ቅዱሳን ወሰዱ አንልም፡፡ ለምሳሌ ጌታ መጥምቁ ዮሐንስን ‹የሚያበራ መብራት ነበር ፤ በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ› ሲለው ወንጌላዊው ደግሞ ‹‹እርሱ ስለ ብርሃን ሊመሰክር መጣ እንጂ ብርሃን አልነበረም›› ብሎታል፡፡ የማንን እንቀበል? የጌታችንን ንግግር ወይስ የወንጌላዊውን? ዮሐንስ ብርሃን ነው ወይንስ አይደለም? መልሱ ግልጥ ነው ዮሐንስ ብርሃን ነው ፤ የዮሐንስ ብርሃንነት ግን ከክርስቶስ ብርሃንነት ጋር ሲተያይ የሻማና የፀሐይ ብርሃን ያህል ነውና ብርሃን አልነበረም ተብሏል ብለን እንረዳዋለን፡፡(ዮሐ. 1፡8 ፤ 5፡35)
ይቀጥላል.....
18
12
1September 1, 2026 1.5K 17