#ኦርቶዶክሳውያን_ለቅዱሳን_ለምን_ይዘምራሉ?
በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ክፍል ፩
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት ብዙ መገለጫዎች አንዱና ዋነኛው ‹ምስጋና የሚገባውን› እግዚአብሔርን ሳታቋርጥ የማመስገን አገልግሎትዋ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ለማመስገን ለዓመታት የዜማ ስልት ተምረው የተመረቁ የስብሐተ እግዚአብሔር ሊቃውንት ያሏት ይህች ቤተ ክርስቲያን ዝማሬዋ ፣ ማሕሌትዋና ቅዳሴዋ የሃያ አራት ሰዓታት ጊዜ የማይበቃው ፣ ለሰዓት ሲባል በንባብ እየተባለ ፣ ዜማው እያጠረ የሚተው በመሆኑ ፀሐይ በማይጠልቅበት በዘላለማዊው መንግሥት ለማመስገን ዝግጁ ሆና የምትጠባበቅ ቤተ ክርስቲያን ያሰኛታል፡፡ ከዚህ እንደ ባሕር ጥልቅ ከሆነው ስብሐተ እግዚአብሔር ጋር የእግዚአብሔር ቅዱሳንንም በሰፊው ታመሰግናቸዋለች፡፡
በዚህች አጭር ጽሑፍ ምስጋና የባሕርይ ገንዘቡ የሆነው እግዚአብሔር ከሆነ ፍጡራን ለሆኑ ለቅዱሳን ሰዎች ፣ ለቅዱሳን መላእክትና ለድንግል ማርያም የሚዘመረው መዝሙርና የሚቀርበው ውዳሴ ምን ያህል ተገቢ ነው? ለቅዱሳን መዘመር ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ተገቢ ነው ወይ? የሚለውን እንመለከታለን፡፡
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሳስብ በመጽሐፍ ቅዱስ ወደር ያልተገኘለትን ዘማሪ ለመጠየቅ ወደድኩ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በስሙ መቶ አምሳ መዝሙራት የተጻፉለት ፣ ራሱ ሰማኒያ ሰባት መዝሙራትን የዘመረና በሥሩ ያሉ መዘምራን ደግሞ አብረውት ብዙ መዝሙራትን የዘመሩበት የዝማሬ ባለ ጠጋ ንጉሥ ዳዊትን ‹‹እውነት ለፍጡራን ምስጋና ይገባል ወይ?›› ብዬ ልጠይቀው አስቤ ወደ መዝሙረ ዳዊት ገሰገስኩ፡፡
ፈጣሪ እንደ ልቤ ያለው ዳዊት የልቤን ማን እንደነገረው እንጃ የእኔን ጥያቄ ለመመለስ ቸኩሎ ጠበቀኝ፡፡ ገና የመጀመሪያው መዝሙሩን ‹‹ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሔደ ፣ በኃጢአተኞች መንገድ ያልቆመ ፣ በዋዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ›› ብሎ ጀምሮት አገኘሁት፡፡ (መዝ. 1፡1) ዳዊት በዚህ ዝማሬው ‹ምስጉን ነው› ያለው ፈጣሪን ነው ወይንስ ፍጡርን? እግዚአብሔርን ነው እንዳልል ‹በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል› ይላል፡፡ ስለዚህ ዳዊት ዝማሬውን የጀመረው ‹በክፉዎች ምክር ያልሔደ ፣ በኃጢአተኞች መንገድ ያልቆመ ፣ በዋዘኞች ወንበር ያልተቀመጠ›ን ሰው በማመስገን ነው፡፡
ወደ መዝሙሩ ስገባ ዳዊት ምስጋናውን ሰፋ አድርጎ ‹ለቅኖች ምስጋና ይገባቸዋል› ‹ለችግረኛ የሚያስብ ምስጉን ነው› ‹አንተ የመረጥከው በአደባባዮችህም ለማደር የተቀበልከው ምስጉን ነው› ‹እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው› ‹እልልታን የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው› ብሎ ከግለሰቦች አልፎ ሕዝብን ሲያመሰግን አገኘሁት፡፡ ከሁሉ ያስደነቀኝ ግን ‹‹መተላለፉ የቀረችለት ፣ ኃጢአቱ የተከደነችለት ሰው ምስጉን ነው›› የሚለው ዝማሬው ነው፡፡ ኃጢአቱን እግዚአብሔር ይቅር ያለውና በደሉን ፈጣሪ የሸፈነለት ሰው በታላቁ ዘማሪ በዳዊት አንደበት መዝሙር ከተዘመረለት በሃሳብዋ እንኳን ኃጢአትን ስላልሠራችው ድንግል ምን ዓይነት መዝሙር ይዘመርላት ይሆን?
ይቀጥላል.....
109
18
1
1August 31, 2026 4.4K 47