እኔን ያስደነቀኝ...
እመቤቴ ሆይ! እኔን ያስደነቀኝ ከሙታን መካከል ተለይተሽ መነሣትሽ አይደለም፤ ትንሣኤና ሕይወትን በመውለድሽ ነው እንጅ። ሞት በሠለጠነበት ማኅፀን የሕይወት መገኘት እንደምን ይደንቃል?!
ድንግል ሆይ! ወደ ሰማይ ከመውጣትሽ ይልቅ የሰማይ ሁለተኛ ተብለሽ መጠራትሽ ይደንቀኛል። ማሕደረ መለኮት በመሆኑ ምድርን ሰማይ ሰማይን ምድር ያደረገ ሰውነትሽ በምድር ተወስኖ ሊኖር እንደምን ይቻላል?!
እመብርሃን ሆይ! ልጅሽ የጽድቅ ብርሃን ነው አንች ደግሞ የብርሃኑ መገኛ የፀሐይ ክበብ ነሽ፤ የፀሐይ ክበብ ለጊዜው በተራሮች ራስ ቢጋረድ መልሶ ላይወጣ ኖሯልን? ያንችም ትንሣኤ እንደዚያ ነው።
ለጊዜው ሰውነትሽ በመቃብር ውስጥ አደረ ነገር ግን በምሽት የጠለቀችው ፀሐይ በማለዳ እንድትወጣ ያንችም ሰውነት ከመቃብር ወጣ።
እመ አምላክ ሆይ! አምላክን የዳሰሱ እጆች፣ መለኮት የተቀመጠባቸው ጉልበቶችሽ፣ ጌታዬ የጠባቸው ጡቶችሽ በመግነዝ እንደታሰሩ ሊቀር ይገባልን? ገፀ መለኮቱን ያዩ ዐይኖች በሞት እንደተከደኑ ትንሣኤ ዘጉባኤን ይጠብቃሉን? ይህስ አይደለም እመቤቴ በሞት ሥልጣን ሥር አይደለችም።
የጌታዬ እናት ሆይ! ጥንቱንስ ቢሆን የታቦት ማደሪያው በመቃብር ውስጥ ነውን? ቃሉ የተጻፈባትን የሙሴ ጽላት በመቃብር ውስጥ አለች ብሎ የሚያምን የተረገመ ነው። የአሮን በትር የዘለዓለም የክህነቱ ምልክት ሆና በመቅደስ ልትኖር ከተገባት የሐዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህናት የ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ንጉሠ ነገሥት ተብሎ የተሾመባት አማናዊቷ በትረ አሮን በሰማዩ መቅደስ በሕይወት ልትኖር አይገባምን?
በነገራችን ላይ ይህንን ታሪክ አምኖ ለመቀበል ከሐዋርያት በጥምቀት መወለድና የሰማዩ የቅዱሳን ኅብረት አባል መሆን ግድ ይላል። ቤተ ክርስቲያናችን የሰማዩ የቅዱሳን ጉባኤ አባል ስለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተነሥታለች፣ ወደ ሰማይ ዐርጋለች ብላ ታምናለች። በሰማይ ያሉ ቅዱሳን እያሸበሸቡ እየዘመሩ ተቀብለዋታል። ይህ በዓል በታቦተ ጽዮን ፊት ሲዘምር ያየነው ዳዊት የዘመረበት ዕለት ነው። ያኔ የበፍታ ኤፉድ ለብሶ የዘመረውን መዝሙር 2 ሳሙ. 6፥14ዛሬ የጽድቅ ካባ ደርቦ ዘመረው። ያኔ የድንግል ማርያም ምሳሌ ለነበረችው ታቦት የዘመረውን መዝሙር ዛሬ በአማናዊቷ ታቦት ፊት አቀረበው።
እኔን የሚያስደንቀኝ የእመቤታችን ምሳሌ በነበረችው መቅደስ ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ሁሉ ዛሬ በአማናዊቷ መቅደስ ፊት ለፊት ቆመው ለማገልገል መብቃታቸው ነው። ሊያዩአት ይመኙ ለነበሩ ሁሉ ዛሬ ተነሥታ በግልጥ አዩአት። ለ እመቤታችን ከተደረገው ይልቅ ለቅዱሳን የተደረገላቸው ብዙ ነው።
የእናቱን ትንሣኤ እንደ ልጇ ትንሣኤ አድርጋችሁ የምታከብሩ የጥምቀት ልጆች ሁላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ወላዲተ አምላክ ማርያም ዐርጋለች።
ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መልአክ!
133
33
10
5August 22, 2026 12.9K 148