አንዱን ወዳጄን በጨዋታ መሃል «ማሻ አላህ በጣም አምሮብሃል!» አልኩት። እርሱም ፈገግ ብሎ እንደ ቀልድ…

አንዱን ወዳጄን በጨዋታ መሃል «ማሻ አላህ  በጣም አምሮብሃል!» አልኩት። እርሱም ፈገግ ብሎ እንደ ቀልድ «ሰሞኑን ለይል ላይ ቆም እያልኩ ነበር፤ ምናልባት እሱ ይሆናል» አለኝ።

እውነቱን ነው... ቀልድ ቢመስልም ጥልቅ እውነት አለው። የለይል ሶላት በፊት ላይ የማይደበቅ፣ በልብ ውስጥም የማይጠፋ ልዩ «ኑር» ያጎናጽፋል።

ታላቁ ታቢዒይ ሐሰን አል-በስሪ «የለይል ሰጋጆች ፊታቸው ከሁሉ በላይ እንዲህ የሚያበራው ለምንድን ነው?» ተብለው በተጠየቁ ጊዜ፤ «በሌሊት ጨለማ ከአል-ራሕማን ጋር ለብቻቸው ተገናኙ፤ እርሱም ከራሱ ብርሃን አለበሳቸው» በማለት የመልካቸውን ሚስጥር ገልፀውታል። በእርግጥም ፈጅርን በጀመዓ ተነስቶ የቀኑን በረካ የተጎናጸፈ ሰውና አርፍዶ በስንፍና የነቃ ሰው የቀን ውሏቸው ፈጽሞ አንድ አይሆንም። ሌሊቱን በከፊልም ቢሆን ከፈጣሪው ጋር ተነጋግሮ ያነጋና በእንቅልፍ ማዕበል ተውጦ ያደረ ሰው ፊታቸው እኩል አይፈካም።

ጉዳዩ የረጅም ሰዓታት ድካም ሳይሆን የቁርጠኝነትና የፍላጎት ጉዳይ ነው፤ ከፈጅር አዛን ቀደም ብለን አስር ደቂቃ እንኳ ብንነሳ፣
ልባችንን ሰብረን የምንሰግዳቸው ሁለት ረከዓቶች የልብን ሰላም፣ የቀንን ስኬትና የፊትን ብርሃን ለመላበስ በቂ ናቸው።

Abu sufyan
October 23, 2026 88