"ፍርሀትን ራሱን ማርበድበድ"
ያዕቆብ ብርሀኑ
ይህችን ዓለም አንቀጥቅጦ የሚገዛት ፍቅር፣ ገንዘብ፣ ሞት፣ ስልጣን ወይስ ፍርሃት? መልሱ ሙዝ የመላጥ ያህል ቀላል ነው፡፡ ይህችን ዓለም በበላይነት የሚያስተዳድራት ፍርሃት ነው፡፡ ከስልጣን መውረድን መፍራት፣ ውርደትን መፍራት፣ እጦትን መፍራት....ፍርሃት፣ ፍርሃት፣ ፍርሃት... ብዙ መልኮች ያሉት ፍርሃት፡፡
ራሳችሁን ነፃ አድርጋችሁ ይህችን ግብስብስ ዓለም ብትመለከቷት፣ ሰብዓዊያን በሙሉ ይህን የፍርሃት ነውጥ በመሸሽ፣ እንደ ዶሮ ጫጩት ሲተራመሱ ማየት ትችላላችሁ፡፡ ሌላው ቢቀር የኤሊ ቆዳ ሻካራነት ስያሜ ማጣት ቢያሳስበን መልስ ለመሻት ‹‹በድሮ ጊዜ ኤሊ ከአእዋፋት ጋር ለግብዣ ሰማይ ቤት ተጠርታ...›› የሚል ለዛ ቢስ ተረት መፈጠሩን ወደድን፡፡
እንዲህ ከሆነ የዚህች ዓለም ጌታን ማንነት ጥያቄ ለመመለስ አዕላፍት መላምታዊ መልሶች ቢፈጠሩ የሚደንቅ አይሆንም።
ለሕይወት የዋህ አረዳድ ያለው አዕምሮአችን እንጂ ኃያል አስመስሎ የሚያሳየን፣ የሰው ልጅ እኮ ፈሪና ድንጉጥ ፍጡር ነው፡፡ ንጉሥ ቄሳር ካሊጉላ፣ በተውኔቱ መሃል በአንድ ቃለ ተውኔቱ ላይ፡- "ፍርሃት በካባው ውስጥ ያለውን ሰው ማንነት ያሳያል፡፡" ይላል፡፡
ለመሆኑ የምንፈራው ምንድን ስለምንስ ነው? ኢየሱስ በዚያች የጸሎተ ሐሙስ አመሻሽ ‹‹አባት ሆይ ፈቃድህ ቢሆን ይህቺ ጽዋ ከእኔ ትለፍ፡፡›› እንዲል ወደ አብ እንዲጮህ የገፋፋው ምክንያት በእርግጥ እርሱ ፍርሃት አልነበረምን? ያለ የጅራፉ ንቅሳት፣ ያለ የችንካሩ ሕማም አዳኝነቱስ የሚቻል ነውን?
እንደ አቡነ አትናቲዎስ፤ (ከ327-373 ዓ.ም ግብፅ አቡነ ሰላማን ቀብተው የላኩት) መላውን ዓለምን መቃወሙስ ይቅር፡፡ እንዴት ሰው በማያምንበት ነገር ላይ የቅርብ አለቆችን እንኳን መቃወም ይሳነዋል? በ325 ዓ.ም በኒቂያ ጉባኤ “ክርስቶስ ሰው እንጂ አምላክ አይደለም” የሚለው የአርዮስ አስተሳሰብ ተወገዘ፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ የጳጳሱ አቡነ እስክንድርን ህልፈት ተከትሎ፣ አቡነ አትናቲዮስ መንበረ ስልጣኑን ተረከቡ፡፡ ጥቂት ዓመታት ቆይቶ አርዮስ የነገሥታቱን ይሁኝታ በማግኘት አቡነ አትናቲዮስን ለብቻቸው በደሴት ውስጥ አሳሠራቸው፡፡ በዚህ ወቅት ከአንድ ወዳጃቸው ‹‹The whole world is against you›› በሚል ለተላከላቸው መልእክት ሲመልሱ ‹‹If the world goes against the truth, then Athunasius will goes against the world›› ብለዋል፡፡ ‹‹ዓለም እውነቱን መቃወምን ከመረጠ አትናትዮስ ዓለምን ይቃወማል›› እንደማለት፡፡ የብርሃኑ ድንቄ አልቦ ዘመዳዊ ‹‹እምቢ አሻፈረኝን ካልተለማመድክ መኖርን አታውቃትም፡፡›› ገደምዳሜ ምክር እዚች ጋ በገቢር ይሠራል፡፡ ግን ስንቶቻችን መላው ዓለም ቀርቶ በቅርብ አለቆቻችን፣ አስሮ ባስቀረን ፍርሃታችን ላይ እምቢ አሻፈረኝ እንላለን?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ሰው ሰው የመሆን ህሊናውን ያገኘው በመተላለፉ አመጽ ውስጥ በበለስ ፍሬዎች መካከል ነበር፡፡ ለዚህም አሻፈረኝ ባይነቱ ማርና ወተት ከሚፈስባት ኤደን ገነት ወደ እሾህና አሜኬላ የሚበቅልባት ምድር ተግዟል፡፡ እዚች ጋ ቆም ብለህ የጆን ስትዋርት ሚልን ‹‹lt is better to be a human being dissatisfied than a pig satisfied. Better to be Socrates dissatisfied than a fool satisfied. ›› የምትል አባባል አስበህ እንኳንም አትልም!
ፍርሃት ግን መልኩ ገጹ፣ መከሰቻ ግብሩ እልፍ ትዕንግርት ነው፡፡ ቪንሰንት ቫንጎ በጥቅምት 2፣ 1884 እ.ኤ.አ ለወንድሙ ቲዮ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ እንዲህም አለ የሚያስብል የሠዓሊንን የልሙጥ ሸራ ፍርሃት አንስቷል፡፡
<<<If one wants to be active, one mustn't be afraid to do something wrong sometimes, not afraid to lapse into some mistakes.... Many painters are afraid of the blank canvas, but the blank canvas IS AFRAID of the truly passionate painter who dares and who has once broken the spell of «you can't.» Life itself likewise always turns towards one an infinitely meaningless, discouraging, dispiriting blank side on which there is nothing, any more than on a blank canvas.»
በእርግጥም ደፍረው የመጀመሪያውን የብሩሽ ጥፊ እስኪያሳርፉበት ውጥሩ ሸራ እንኳን አተያዩ የጠበኛ፣ የወደረኛ ዓይነት ይሆናል፡፡ የሥነ ተረቱ ሰው ጆሴፍ ካምቤል ‹‹ሕይወት ራሷ የምትጀምረው ከአመጽ (act of disobidence) ነው›› ይላል፡፡ ትልቁ ጠላታችን ያለው እኛነታችን ውስጥ ነው፡፡ የማንነታችን አክናፍ በእጆቻችን እንዳንሠራ መሰናክል የሆነን ትልቁ አውሬ ያሸመቀው እኛነታችን ተጣብቆ ነው፡፡ መፍራትስ ሺኅ የገደለውን አይደለም፡፡ ፍርሃቱን ያሸነፈውን እንጂ...ፍርሃቱን ጠፍንጎ አስሮ ለራሱ ለፍርሃት ላስረከበ ለእርሱ እንኳን ውጥሮ ሸራ ምድር ትርበታበታለች፡፡ በማይናወጡ ጽኑ ዓይኖች አንበሳውን መማተር የሚችሉ የማሳያ ጎሳዎች ያለምንም መሰንዘር ከአንበሳው መንጋጋ ስጋን ያስጥላሉ፡፡ ስብሃት ከሕልፈቱ በፊት እንደከተበልን በተለፈፈላት መልዕክቱ ‹‹ተዘጋጀህም አልተዘጋጀህም ጥሪው እንደሁ አይቀርልህ..›› ብሏል፡፡ እናስ ድፈር እንጂ ባይሆን የምር ኖረህ ሞትህ የጀግና ማድረግ ነው፡፡ ራሱ አልበርት ካሙ በ‹‹Happy death ልብወለዱ እንደነገረን አንዳንድ ጊዜ ራስን ከማጥፋት ይልቅ ራስን ማሰንበት የበለጠ ጀግንነት ይፈልጋል፡፡
@zephilosophy




