ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት ከካህናት አለቆች መካከል አንዱ ብትሆኑ፤ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME

ኢየሱስ በምድር በነበረበት ወቅት ከካህናት አለቆች መካከል አንዱ ብትሆኑ፤ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ መሆኑን ብትረዱ፣ ነገር ግን መምጣቱ በሞቱ ሰውን ለማዳን እንደሆነ ቢገለጥላችሁ የፋሲካው ሰሞን በነበረው ሁነት ምን አይነት ሚና ይኖራችሁ ነበር? አለጥፋቱ ወደ መስቀል ከመላክ የዘለለ ሌላ አማራጭ ይኖራችኋል? እርሱ አይሙት እኔን ጨምሮ መላው የሰው ልጆች ወደ ጥፋት ይሂዱ ብላችሁ ትበይኑ ነበር? ወይንስ ጻድቁን ወደ መስቀል እንዲሄድ ትፈቅዳላችሁ?

በጊዜው የነበሩት የካህናት አለቆች ስላላወቁትና ስላልተቀበሉት በቅናት አሊያም ለሕጋቸው ወግነው ለሞት አሳልፈው እንደሰጡት ሁሉ እኛም ክርስቶስ መሆኑ አውቀነው እንኳን ቢሆን እንዳይሞት የመተው ድፍረት እናገኝ ይሆን? ምናልባት እንደ ጲላጦስ እጃችንን ከመታጠብ የዘለለ ለፍትህ የሚያቆም ጥሩነት የሚገኝብን አይመስልም።

በኢየሱስ መሞት በወቅቱ የነበሩ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ማናችንም በእነርሱ ወንበር ብንሆን ከተጠያቂነት የምንድን አልነበርንም። እንደውም የመሲሑን መሞት አስፈላጊነት አስቀድመን ተረድተን ከሆነ ከፈራጆቹ ግንባር ቀደምነት የሚመልሰን ያለ አይመስልም። እናም የመስቀሉ ሞት በአይናችን ፊት ውልብ ባለ ጊዜ ራሳችንን ንጹህና ምስኪን አድርገን እነኛን የካህናት አለቆችና ሹማምንቶችን ከፉ አድርገን አንመልከታቸው። እኛም ከእነዛ ክፉነት  የተለየ ብዙም ደግነት አይኖረንም ነበር። እርሱን ከመግደል ወይም አሳልፎ ከመስጠት የሚመለስ አቅም የለምን። እርሱ ግን ይህን ሁሉ እያወቀ ለእኛ ከመሞት ወደኋላ አላለም።

ሁለት የተቃረኑ እውነቶች አሉ፤ እኛ ኢየሱስን ከመግደል የማይመለስ ራስወዳድነት፤ እርሱ ለገዳዮቹ ከመሞት የማይመለስ ፍቅር! ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም!

መልካም የትንሣኤ መታሰቢያ በዓል
❤8👍3🥰1👏1
April 12, 2026 298 1