አመስጋኝ ነኝ" ን የጻፍኩበት ሰሞን.... ጥሩ ቤተሰባዊነት የናኘበት ወዳጅነት ነበረን፤ ለጊዜው ስሟን… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME

yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶችአመስጋኝ ነኝ ዙሪያ ገባውን ስመለከት ልዘነጋቸው በማልችላቸው ከጌታ በተሰጡኝ በርካታ ወዳጆች ተከብቤ ራሴን አገኛለሁ። እነኚህ ወዳጆቼ ወዳጆነት ምን እንደሆነ ኑረውት አሳይተውኛል። የወዳጅነት ትርጉሙ በቅጡ ባልገባኝና ባልተረዳሁበት የልጅነት ወቅት ሳይቀር የወዳጅነትን ብርታት አመልክተውኛል። አንዳንዶች በደከመኝና አቅም ባጣሁበት የሕይወት ምዕራፍ ከጎኔ ተገኝተውልኛል። እዚህ ግባ የማልባልና አባ ከና…
"አመስጋኝ ነኝ" ን የጻፍኩበት ሰሞን....

ጥሩ ቤተሰባዊነት የናኘበት ወዳጅነት ነበረን፤ ለጊዜው ስሟን ከማልጠቅሳት "ጓደኛዬ" ጋር። ጓደኝነቱ ሌላ ይዘት አልነበረውም፤ በቃ ጥሩ ወዳጆነት ብቻ። ከዛ ባለፈ በተፈጠረልኝና ባገኘሁት አጋጣሚ በሕይወቷ ላይ በጎ አሻራ እንደነበረኝ አውቃለሁ።

ታዲያ በአንድ አጋጣሚ ከዚህች ወዳጄ ጋር በቅርበት የምናሳልፍበትን ሁኔታ መፈጠሩን ተከትሎ የተለየ ነገር ማስተዋል ጀመርኩ። በሕይወቴ እንኳን ቅርብ ከምለው ሰው ይቅርና ለእኔ ጥሩ እይታ የላቸውም ብዬ ከማስባቸው ሰዎች ገጥሞኝ የማላውቀው አይነት ባህሪ ተመለከትኩ። አክብሮት አጥነት በተላበሰ አኳሃን ያሳየችኝ ድርጊቶች አስቀየሙኝ።

ተቀየምኩ፤ የቅርብ ከምንለው ሰው ያልጠበቅነው ነገር ስንመለከት ሊሰማን የሚችለው አይነት ስሜት ተሰማኝ። ክፉም ሆነ ደግ አልተናገርኩም። ውስጤ ያስከፋኝን ነገር ይዤ ወደ ራሴ መለስ ማለትን ሞከርኩ። ቀጥሎ ልቤ ካዘነባት ልጅ ይልቅ በዙሪያዬ የከበቡኝን ወዳጆቼንና ደግነታቸውን መቁጠር መረጥኩ። ቆጥሬ የማልጨርሳቸው መልካምነታቸው ከአእምሮዬ በላይ የሆኑ ወዳጆቼ ተዘልለው ታዩኝ።

የአንዳንዶቹ ደግነት ድንቅ ነበር፤ ተርኬ የማልዘላቃቸው፤ አውርቼላቸው የማይወጣልኝ ወዳጅነት። ያልተገደበ ፍቅር፣ ያልተቆጠበ መልካምነት፣ ያልደበዘዘ ትኩረት፣ በእኔ መለዋወጥ ያልተለወጠ እምነት ያሳዩኝ ደጋግ ነፍሶች።
እናም በመገረም ብዕሬን አንስቼ መጻፍ ጀመርኩ "አመስጋኝ ነኝ...." ብዬ።

በሂደት ውስጤ የነበረው ቅሬታ ተጠራርጎ ሲሄድ ተሰማኝ። እንደውም ለዚች ወዳጄ ከበፊቱ የተሻለ ፍቅርና ርህራሄ በውስጤ አደረ። ችግሩ እኔ ሳልሆን እርሷ መሆኑን ለማስተዋል አቅም አግኝቻለሁና።

ወዳጆቼ በሚገጥሙን ጉራማይሌ መልክ ባላቸው ሁነቶች ውስጥ በምንመለከተውንና በምንሰጠው ግብረ መልስ ላይ ጠንቃቆችና ብልህ መሆን ጠቃሚ ነው። የሚጠሉን ሰዎች ሲገጥሙን የሚወዱንን እንቁጠር። ሕይወት ጨለምለም ያለ ገጽታዋ ሲበረታ ጭልጭል በሚለው ብረሃን ላይ አይናችንን እናድርግ። ስላልሆነና ስለጎደሉ ነገሮች ከማጉረምረም ስላገኘናቸውና ስለተሳኩልን ነገሮች እናመስግን። በተቻለ መጠን በአሉታዊ የሕይወት ንጽረት ላለመወሰድ እንጠንቀቅ። አዎ የምናየውን እንምረጥ!

መልካም ዕለተ ሰንበት!
❤9🥰4
April 13, 2025 429