አመስጋኝ ነኝ ዙሪያ ገባውን ስመለከት ልዘነጋቸው በማልችላቸው ከጌታ በተሰጡኝ በርካታ ወዳጆች ተከብቤ ራሴን… — yero's reflections/ የየሮ ንጽረቶች — TG.ME

አመስጋኝ ነኝ

ዙሪያ ገባውን ስመለከት ልዘነጋቸው በማልችላቸው ከጌታ በተሰጡኝ በርካታ ወዳጆች ተከብቤ ራሴን አገኛለሁ። እነኚህ ወዳጆቼ ወዳጆነት ምን እንደሆነ ኑረውት አሳይተውኛል። የወዳጅነት ትርጉሙ በቅጡ ባልገባኝና ባልተረዳሁበት የልጅነት ወቅት ሳይቀር የወዳጅነትን ብርታት አመልክተውኛል።

አንዳንዶች በደከመኝና አቅም ባጣሁበት የሕይወት ምዕራፍ ከጎኔ ተገኝተውልኛል። እዚህ ግባ የማልባልና አባ ከና የሚለኝ ባልነበረበት ወቅት ፈልገውኛል፤ ጊዜና ትኩረታቸውን ችረውኛል። የሕይወት ዳገትን ለመውጣት አቅሜ ሲዝል ደግፈውኛል፤ ስጠፋ አልረሱኝም፤ ተደብቄ ላዘግም ስፈቅድ ለፈቃዴ ሊተዉኝ ስላልፈቀዱ ከዙሪያዬ አልተለዩም።

አንዳንዶች ፈታኝ በሆኑ የሕይወቴ ወቅቶች በሁሉ ነገር ከጎኔ ለመሆን ፈቅደዋል። በፍቅር ልባቸውንም ቤታቸውንም ከፍተውልኛል፤ ሕይወታቸውን ሳይቀር ቆርሰው ለማከፋል ፈቅደዋል። አንዳንዶች የመወደድ ትርጉሙ በማይገባኝ የአፍላነት ዕድሜዬ ሳይቀር ያልተገደበና ያልሳሳ ፍቅር ለግሰውኛል። ምላሼ በዛ ልክ ባይሆንም፣ የፍቅራቸውን ትርጉም የሚገባው አእምሮ ባይኖረኝም፣ የፍቅራቸውን ጥልቀት የሚረዳ ልብ ባልገዛም ፍቅራቸውን አልተቆጠበም። እኔን ከመውደድ ሆነ ለእኔ ፍቅር ከመስጠት አልቦዘኑም። ቁልምጫቸው፣ የስስት አይናቸው፣ አክብሮታቸውና አብሮነታቸው ያስገርመኛል።

የሕይወት መንገዳቸው ለእኔ ሲሉ ለመቀየር የፈቀዱ፤ በሕይወት መንገድ ከእኔ ጋር ለማዝገም እነርሱ ባልመረጡት መንገድ ለመጓዝ ያላመነቱም ነበሩ። ለእኔ ብለው ትላልቅ "risk" የወሰዱ፣ ሊያስኮንናቸው ሊያስወቅሳቸውና ዋጋ ሊያስከፍላቸው በሚችል ጎዳና ለመገኘት የደፈሩም አልጠፉም።

ሌሎች ደግሞ በብዙ ነገራቸው አምነውኛል፤ ቤታቸውን ከፍተው ጓዳ ጎድጓዳውን ሳይቀር አሳይተውኛል።  በትላልቅ የሕይወት ጉዳዮቻቸው ከእኔ ምክር ተቀብለዋል፤ ከእኔ ለመማር መርጠዋል። ምክሬን ሰምተው  ለመተግበር ልባቸው ፈቅዷል። አንዳንዶች ቁጣዬንና የፊቴን መጥቆር ሳይቀር አይተው አቅጣጫቸውን አስተካከለዋል፤ እኔን ላለማስቀየም ፋላጎታቸውን ገተዋል። በእርግጥም አክብረውኛል!

በሕይወት ውስጥ በሰው ተከብቤ ሰው እንዳጣው በተሰማኝ ወቅት፤ ላወራና ልተርከው በሚቸግረኝ ምጥ ውስጥ አንዳንዶች ሳልነግራቸውና እገዛ ሳልጠይቃቸው "እኔ አለውልህ" ብለው በብቸኝነት የጠወለገውን እኔነቴን በአብሮነታቸው አለምልመውት ከልብ ተወዳጅተውኛል።

አቋሞቼ አፈንጋጭ ሁነው ሰፈር በረበሹ ወቅቶች እኔን ለመምከር ያልቦዘኑ ብዙ ናቸው። ምክር ለማስማት ባስቸግርም "ጉዳዩ" ብለው አልተዉኝም።አዎ፤ ደስታዬን ለመመልከት፤ ተሽዬ እንድገኝ ስለሚሹ። በዚህ ሁሉ ግን ስለእኔ መልካሙንና ደጉን ከማውራትም አልተቆጠቡም። በሌለሁበት ስለ እኔ ተከራክረዋል፣ አንዳንዶች ውግንናቸው ከሰው እስከመቀያየም አድርሷቸዋል። "ለምን ቢባል?" ስሜ በክፉ እንዳይነሳ፤ አለስም ስም እንዳይሰጠኝ። ራሴን በአሉታዊ መልክ ለመሳል በፈቀድኩባቸውና ለመጥፎ ትችቶች ራሴን ባጋለጥኩባቸው ወራቶች ሳይቀር በጓዳ እየመከሩኝና እየገጸጽኝ በአደባባይ ተማጉተውልኛል።

ለራሴ ከምሰጠው ዋጋና ግምት በላይ የተመኑልኝ፣ ያበረታቱኝ፣ ትንሿን ጥረቴን በማደናነቅ ለበለጠ ትጋት ያነሳሱኝም ጥቂት አይደሉም። የረሳኋቸውንና ችላ ያልኳቸውን ህልሞቼን ሳይቀር እንደዋዛ እንዳልቆጥር ጊዜ ጠብቀው የሚቀሰቅሱኝ፤ በራሴ ላይ ያለኝ እምነት በተመናመነበት ወቅት ሳይቀር በእኔ ላይ ያለቸው እምነት እንድበረታ አቅም የሆነኝ ወዳጆች.....

አዎ፤ አውርቼ የማልዘልቃቸው ተርኬ የማልጨርሳቸው በረከቶቼ ብዙ ናቸው። በዘመን ያልተለወጠ ጓደኝነታቸው ያስደሰተኝ፤ በመከፋቴ የተከፉልኝ፤ አሰልቺ በሆኑ የሕይወት ገጽታዎች ሳይሰለቹ ጆሮቸውንና ልባቸውን የሰጡኝ፣ በደስታዬ ከእኔ በላይ የተደሰቱ፤ ፍቅራቸውንና ቅርበታቸውን በእንባቸው ሳይቀር የመሰከሩ። ከእኔ ሊቀበሉ ሲገባቸው ከጉድለታቸው ያካፈሉኝ በዘመንና በሁኔታ ተፈትነው ያለፉ ወዳጆቼ እልፍ ናቸው ። በዘር፣ በቀለም፣ በሐይማኖትና በሌሎች ነገሮች መለያየታችን ለወዳጅነት እንቅፋት ያልሆነብን ብዙ  ወዳጆች....
ስለ ሁሉ አመስጋኝ ነኝ።
ስለዚህ ሁሉ  እጅግ አድርጌ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ!
እንዲህ ብዬም እዘምርልሃለሁ

እግዚአብሔር ሆይ ተመስገን ተመስገን ተመስገን
የሰጠኸኝ እልፍ ወገን
ከአንተ ያገኘኋቸው ወዳጆቼ ብዙ ናቸው
ባርካቸው ባርካቸው!
❤11👍1
February 11, 2024 803 5