ካብ ለካብ" ++++++ (በአንድ የፈረንጅ ቲክቶክ ቪዲዮ መነሻነት የተጻፈ ቀላል ታሪክ)… — ወግ ብቻ — TG.ME

"ካብ ለካብ"
++++++
(በአንድ የፈረንጅ ቲክቶክ ቪዲዮ መነሻነት የተጻፈ ቀላል ታሪክ)
------------

አልጋው ላይ ተኝቶ አጫጭር ቪዲዮዎችን እያፈራረቀ ሲመለከት ስልኩ ጠራ።

የደዋይዋን ስም ሲያይ ፈገግ አለና በሁለተኛው ጥሪ አነሳው።

«ሄይ የኔ ፍቅር። እንዴት ዋልክልኝ? የት ነህ?» አለችው።
«ሄይ ማሬ... ቤቴ ነኝ» ብሎ መለሰላት።
«ቤትህ ምን እያደረግክ?»
«ምን አደርጋለሁ?…ዝም ብዬ ስልኬ ላይ ያው በቲክቶክ እየዛግኩ»
«ውይ…ደብሮሃል እንዴ የእኔ ፍቅር?»
«አይ ብዙ አልደበረኝም…»
«ኦኬ…እኔማ የደወልኩልህ ዓለም ሲኒማ ቴአትር ልንገባ እንደሆነ ልነግርህ ነው.. ከዛ በኋላ ደሞ እራት እንበላለን ብለናል፣ ስለዚህ ዛሬ አልመጣም። አርብ ስለሆነ ፈታ ልበል ብዬ እኮ ነው»
«ኦ... እሺ። ኢንጆይልኝ»
‹‹ኢንጆይልኝ ስትለኝ እንዴት ደስ እንደሚለኝ ታውቃለህ አይደል?››
‹‹ለዛ እኮ ነው ሁሌ የምልሽ››
‹‹ሃሃ…የራስህ ብራንድ እኮ ናት…አማእንግሊዝኛ…የእኔ ፍቅር››
‹‹እንዲህ ካበረታታሽኝማ ሳልሰረቅ የአይምሮ ምናምን ሄጄ አስመዘግባታለሁ በቃ…››
«አይ አንተ…! ኤኒዌይ ከእራት በኋላ ደግሞ የሆነ ላውንጅ እንሂድ ማለታቸው የማይቀር ነው… ስለዚህ ስልክ ባላነሳ እንዳታስብ..ጫጫታው አያሰማም››
‹‹አላስብም››
‹‹ደሞ ቤቴ ድረስ የሚያደርሰኝ ሰው ስላለ ምንም ብለህ እንዳትጨነቅ »
«ኦኬ ጉድ… ግን ማን ነው እቤት የሚያደርስሽ?»
«ቤቲ»
«ቤቲ... ?የቷ ቤቲ?»
«ቤቲ ናታ! ቤስት ፍሬንዴ?»
«ማ…?››
‹‹ምን ሆነሃል? ቤቲ ጠፍታህ ነው››
‹‹ አይ…... እ…ኖ…አልጠፋችኝም…ሶ …ቤቲ ታደርስሻለች…አ?»
«አር ዩ ኦኬ የእኔ ፍቅር?››
«አይ አም ፋይን…ያልጠበቅኩት…እሷ…ማለቴ እሷስ አብራችሁ አታመሽም ወይስ...?»
«ታመሻለች ግን እሷ መጠጥ አትጠጣም ስለዚህ ችግር የለውም። አትጨነቅ አልኩህ እኮ»
«እ..አይ… አልተጨነቅኩም... እና አሁን ከ..ከቤ …ከቤቲ ጋር አብራችሁ ናችሁ?»
«አዎ…ተገናኝተናል የሆነ ነገር ልግዛ ብላ ሱቅ ገብታ ነው። አሁን እራሱ መኪናዋ ውስጥ ሆኜ ነው የማወራህ»
«ተይ እንጂ?»
«አዎ…ምነው የገረመህ መሰልክ?»
«አይ ምን ይገርመኛል…? ምንም አልገረመኝም አረ»
«ሃሳብህ የተሰረቀ ይመስላል። ዩ አር ኦኬ አይደል?»
«ኖ ኖ... ደህና ነኝ።»

ለአፍታ ጸጥታ ሰፈነ።

«ኦኬ ስለዚህ በቃ ፈታ ብዬ አመሻለሁ…ነገ ጠዋት ስበር ወዳንተ እመጣለሁ… ስራ አጎሳቆለኝ እኮ ሰሞኑን… እስቲ ዛሬ ይለፍልኝ።»
«ተፍታቺ የእኔ ቆንጆ... ኢንጆይልኝ»
«ታንኪው ናሆምዬ። እወድሃለሁ።»
«እኔም እወድሻለሁ።»

ናሆም ስልኩን ዘግቶ ኮመዲኖ ላይ አስቀመጠና አጠገቡ ወደተኛችው ሴት ዞረ።

ሁለት ትራሶች አነባብራ ቀና ብላ ታየዋለች።

«..ሰላም ናት…ካንቺ ጋር ነኝ ነው የምትለኝ » አላት ፊቱን ቋጥሮ።

ሴቲቱ በሳቅ ፈነዳችና፣

«ሃሃሃ... አለ መኮንን» አለች፡፡
«ምን ያስቅሻል?» ቆጣ ብሎ ጠየቃት፡፡
«ምንም።»
«ሲሪየስሊ ዋት ኢዝ ሶ ፈኒ?»

ሳቋን በእጇ አግታ ታስቀር ይመስል አፏ ላይ አድርጋ፣

«አይ…እንደው ዋሸሽኝ ብለህ እንኳን ልትናገራት እንደማትችል ሳስብ ነገሩ አስቆኝ ነው…›› አለችው ከሳቋ እየታገለች፡፡

‹‹እና ታዲያ እሱ ምኑ ነው የሚያስቀው?›› አላት አሁንም እንደተኮሳተረ፡፡

«...የሚያስቀውማ አንተም እየዋሸሃት መሆኑ ነዋ…እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ አለች አያቴ »

‹‹ኤጭ…እባብ ካብ ምናምን.. እስቲ ዛሬ እንኳን ይሄን ያሮጊት ተረትሽን ተወት አድርጊ…›› ብሎ በብስጭት ተስፈንጥሮ ካልጋው ተነሳ፡፡

----
በዚህችው ቅጽበት በሌላኛው የከተማው ጫፍ ደግሞ እንዲህ ሆነ፡፡

ሰላም ስትነጋገርበት የቆየች ስልኳን ስልቻ የሚያህል ቦርሳዋ ውስጥ ጨመረችና የመኪናውን መሪ በጣቶቹ ወደ ሚቆረቁረው ወንድ ዞረች።

«ጉድ ኒውስ ሃንድሰም» አለችውና ወደኋላ ደገፍ ብላ ተቀመጠች፡፡

‹‹ተሳካልሽ አይደል?›› አላት ሳቅ ብሎ እያያት፡፡
«ድሮስ ! ዛሬ የፈለግንበት ቦታ የፈለግነውን ያህል ማምሸት ከፈለግንም ማደር እንችላለን።»

ሳቁ ደመቀ።

ሰከንዶች እንዳለፉ ፊቷን ጨፍገግ አድርጋ፣

«ግን ቤቲስ?» ስትል ጠየቀችው።
«ስለእሷ አታስቢ…ትንሽ ቆይቼ እደውልላታለሁ፣» አላት ዘና ብሎ፡፡

ግን አሁንም ፊቷ አለመፈታቱን ሲያይ ቁኝ እጁን ወደተጋለጡ ጭኖችዋ ሰደደና፣

«አታስቢ አልኩሽ እኮ…ዋናው ያንቺ ነበር..እኔማ ከናሆም ጋር አመሻለሁ እላታለሁ አለቀ!›› ብሎ ጨመረ፡፡

By Hiwot emishaw

@wegoch
@wegoch
@paappii
😁74❤33
July 8, 2026 6.3K 30