ፖስት ፒል ግዛልኝ" የሚል የጽሁፍ መልእክት ላከችልኝ። የታዘዝኩትን ልፈፅም ፋርማሲ ተገኘሁ። ፓራስታሞል… — ወግ ብቻ — TG.ME

"ፖስት ፒል ግዛልኝ" የሚል የጽሁፍ መልእክት ላከችልኝ። የታዘዝኩትን ልፈፅም ፋርማሲ ተገኘሁ።

ፓራስታሞል ፋላጊው ፥ ኮንዶም ሸማቹ ፥ ቬርሞክስ ገዢው... ከፋርማሲው የሚፈልጉትን ሲወስዱ ከሻጩ ፊትለፊት አቀርቅሬ ቆምኩ። "ምን ልታዘዝ?" ሲለኝ ነበር የባነንኩት። እያማጥኩ "ፖስት ፒል" አልኩ።

ዛሬ ለአራተኛ ጊዜ ፖስት ፒል ገዛሁላት።

አፈቅራታለሁ። ስለ እኔ ስታወራ "የቅርብ ጓደኛዬ ነው" ትላለች። "እንደ ወንድሜ ነው የማየው" ትላለች። "ከንፁህ ጓደኝነት የዘለለ ነገር የለንም" ትላለች። እኔ ግን አፈቅራታለሁ።

እንደማላገኛት እያወቅኩ ሳልማት ኖርኩ። የእኔ ላደርጋት እየተመኘሁ የሌላ ስትሆን አየሁ።

ናቲ በድን እንዳየ አው^ሬ ሲያንዣብብባት "ተጠንቀቂ" ያላልኳት ፈርቻት ነው። የምትፈልገውን እየነገራት ወደሚፈልግበት ነዳት። እንደሚወዳት እየተወነ ፍቅር አስያዛት።

"ናቲ ያደምጠኛል" ትላለች። ናቲ አድማጭ አይደለም። በግራ ጆሮ እየሰማ በቀኙ ያፈሳል። "ጨዋታ አዋቂ ነው" ትላች። ጨዋታ አያውቅም። ቀልዶቹ ያሳቋት ስለወደደችው እንደሆነ አታውቅም። አበባና ቸኮሌት ስለላከላት "ስለ እኔ ደጋግሞ ያስባል" አለች። ስጦታዎቹ ወደ ማረ^ጃ ስፍራው መውሰጃ እንደ ሆኑ አላወቀችም። "ነፃ ሰው ነው" ትላለች። የወ^ሲብ ቀልድ የሚቀልድላት ለእቅዱ እያመቻቻት እንደሆነ አይገባትም።

ናቲ ያደረገላትን ሁሉ አድርጌላት ነበር። ዋጋ አልሰጠችውም እንጂ ስጦታዎች አዝንቤላታለሁ። ቀልዶቼ በፊቷ ሞገስ ባያገኙም ላስቃት ሞክሬያለሁ። አድማጭ መስዬ ባልታያትም የምትነግረኝን ሁሉ ከልቤ ስመዘግብ ኖሬያለሁ።

ልፋቴ ሁሉ "ንፁህ ጓደኛዬ" የሚል ማዕረግ ነው ያስገኘልኝ። "እንደ ወንድሜ የማይህ ጓደኛዬ ነህ" ትለኛለች።

ናቲ አስመሳይ መሆኑን ልነግራት ሳስብ ቀደመኝ። ወደ መኝታ ወሰዳት። ብር አምባሯን ሰበረው። ተኝቷት ሲጠግባት ተዋት።

ናቲ ሲተዋት ሳሚ ተተካ።

"ሳሚ በሃዘኔ ቀን አጠገቤ ነበር" አለችኝ። "ናቲ ሲያስለቅሰኝ ሳሚ እንባዬን አበሰው" አለችኝ። ከሳሚ በፊት ያፅናናኋት እኔ ነበርኩ። ስታለቅስ እንባ ተናንቆኛል። ስታዝን አብሬያት አዝኜያለሁ።

"ከሳሚጋ ተሳሳምን" አለችኝ።
"እንዴት?" አልኳት።
"ናቲ ያደረገብኝን በደል ሁሉ ነገርኩት። ሳለቅስ እንባዬን ጠረገ። በእቅፉ አስገባኝ። አቅፎኝ አለሁልሽ አለኝ። ከዛ..."

የቅናት ጦ^ር ወ^ጋኝ።

ሳቅፋት ከእቅፌ አልሸሸችም? ስታለቅስ አላፅናናኋትም? አለሁልሽ አላልኳትም?

ሳሚ ይተኛታል። እስኪተዋት ድረስ ይተኛታል።
ሳሚ እንደሚንቃት አውቃለሁ። "አከብርሻለሁ" ስላላት ያከበራት መሰሏታል። "እወድሻለሁ" ስላላት የወደዳት መሰሏታል።

ኮን^ዶም አይጠቀሙም። ፖስት ፒልም አይገዛላትም። ይተኛታል ፥ ይሸኛታል።

ከሳሚጋ ከተኛች በኋላ ፋርማሲ ሄዳ ፖስት ፒል መግዛት ያሳፍራታል። "ወ^ሲብ ፈፅሜ እየመጣሁኝ ነው። እንዳላረግዝ መድሃኒት ስጡኝ" ማለት ያሳፍራታል።

ሳሚ ይተኛታል፥ እኔ ፖስት ፒል እገዛላታለሁ።

ፖስት ፒል ስገዛላት እንዴት እንደተዋሰቡ እያሰብኩ እቀናለሁ።

"ንፁህ ወንድሜ ነህ" ትለኛለች። "ጓደኛዬ ነህ" ትለኛች። እንደማፈቅራት ነግሬያት ባላውቅም ማፍቀሬን ታውቃለች።

በወደደቻቸው ወንዶች እንደምቀና እያወቀች አትራራልኝም።በገዛ ስልጣኔ ጨክኜ ልርቃት እንደማልችል እያወቀች በስልጣኗ አታባርረኝም...

ለምን አታዝንልኝም?

By Tesfab Teshome

@wegoch
@wegoch
@paappii
😢54❤28
July 8, 2026 5.2K 16