የእንጨት አምልኮ በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 11፥2 እንዲህ በላቸው፡… — ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics" — TG.ME

የእንጨት አምልኮ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

11፥2 እንዲህ በላቸው፡- «አሏህን እንጂ ሌላን አታምልኩ! እኔ ለእናንተ ከእርሱ የተላክሁ አስጠንቃቂ እና አብሳሪ ነኝ»። أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا اللَّهَ ۚ إِنَّنِي لَكُم مِّنْهُ نَذِيرٌ وَبَشِيرٌ

በኦርቶዶክስ እና በካቶሊክ ክርስትና "ዕፀ መስቀል" የሚባል ስግደት እና አምልኮ የሚቀበል ግዑዝ ነገር አለ፥ "ዕፅ" ማለት "እንጨት" ማለት ሲሆን "ዕፀ መስቀል" ማለት "የእንጨት መስቀል" ማለት ነው። በግሪክ ኮይኔ "ስታውሮስ ክይሎን" σταυρός ξύλον ሲባል ይህ የእንጨት መስቀል የማይሰማ እና የማይለማ እንዲሁ የማይናገር እና የማይጋገር ግዑዝ ነገር ሆኖ ሳለ በኦርቶዶክስ ይሰገድለታል፦
የዘወትር ፀሎት ቁጥር 8
"ዓለምን ለማዳን ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ “ለ”-ተሰቀለበት መስቀል እሰግዳለው"

ለእንጨት መስቀል መስገድ አግባብ ነውን? ዘርዓ ያዕቆብ ከደረሳቸው መጻሕፍት አንዱ "መስተብቁዕ ዘመስቀል" ነው፥ "መስተብቁዕ" ማለት "ልመና" "ጸሎት" ማለት ሲሆን "መስተብቁዕ ዘመስቀል" ማለት "የመስቀል ልመና" ማለት ነው። መስተብቁዕ ዘመስቀል ላይ መስቀል እና ማርያም ከፈጣሪ ጋር ተካክለው ምስጋና እንደሚቀርብላቸው ይናገራል፦
መስተብቁዕ ዘመስቀል ቁጥር 8
"ለእሉ ክልኤቱ ፍጡራን ስብሐተ ፈጣሪ ይደልዎሙ እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ"

"ለእነዚህ ሁለት ፍጥረታት የፈጣሪ ምስጋና ይገባቸዋል፥ በክብር ተካክለዋልና"

"ሁለቱ" የተባሉት "መስቀል እና ማርያም" ሲሆኑ እነዚህ ሁለት ፍጡራን ከፈጣሪ ጋር "በክብር ተካክለዋል" ይለናል፥ ኢየሱስን፦ "ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ(በባሕይርው ከአብ ጋር የሚተካከል)" ሲሉት ሲገርመን ማርያም እና መስቀልን "እስመ ተዐረዩ በክብሮሙ(በክብር ተካክለዋል)" ሲሏቸው አስደመመን። ስለተስተካከሉ ለፈጣሪ የሚገባው የፈጣሪ ምስጋና "ይገባቸዋል" ብለው አረፉት፥ ይህ እልም ያለ ሺርክ ነው። ስብሐት(ምስጋና) ለሦስቱ ማለትም ለእግዚአብሔር፣ ለድንግል እና ለመስቀል እንደሚገባ የዘወትር ጸሎት ላይ ተገልጿል፦
የዘወትር ጸሎት ቁጥር 9
"ስብሐት ለእግዚአብሔር ወወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር"

ትርጉም፦ "ለእግዚአብሔር፣ ለወለደችው ለድንግል እና ለክቡር መስቀሉ ምስጋና ይገባል"

እንደ ሥላሴ አስተምሮት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ፈጽመው ሳይለያዩ እንደሚስተካከሉ ሁሉ እግዚአብሔር፣ ድንግል ማርያም እና መስቀል በክብር ይተካከላሉ፦
ድርሳነ መድኃኔ ዓለም ዘሰኑይ ምዕራፍ 10 ቁጥር 19
"ይህ መስቀል እንደ እግዚአብሔር የከበረ እንደ ድንግል ማርያም ከፍ ያለ ነው፥ ሦስትነታቸው ትክክል የሚሆን እንደ አብ፣ እንደ ወልድ፣ እንደ መንፈስ ቅዱስ ፈጽሞ የማይለይ ነው። እንዲሁም መድኃኒታችን ከእናቱ እና ከመስቀል ጋር ሦስትነታቸው ትክክል ነው፥ እንዲህ እናምናለን እንዲህ እናመልካለን"።

"እንዲህ እናምናለን እንዲህ እናመልካለን" የሚለው ይሰመርበት! "መድኃኒታችን ከእናቱ እና ከመስቀል ጋር ሦስትነታቸው ትክክል ነው" ካለ ሌላ ሥላሴ ሆኑ ማለት ነው፥ በተጨማሪ ማርያምን እና መስቀልን ከእግዚአብሔር ጋር "እናመልካለን" ካሉ ዓይን ያስፈጠጠ እና ጥርስ ያስገጠጠ ባዕድ አምልኮ ነው። "የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፣ አትስገድላቸው፣ አታምልካቸውም" እየተባለ ለማይሰማ እና ለማይለማ፥ ለማይናገር እና ለማይጋገር ለግዑዝ እንጨት ስግደት መስገድ እና አስተካክሎ ማምለክ አግባብ አይደለም፥ ይህ ድርጊት አሳፋሪ እንደሆነም ተገልጿል፦
መዝሙር 97፥7 "ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ" ሁሉ እና በጣዖቶቻቸው የሚመኩ ይፈሩ።
ዘጸአት 20፥4 የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ! አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም።

"ለተቀረጸ ምስል የሚሰግዱ ሁሉ ይፈሩ" የሚለው ይሰመርበት! ለተቀረጸ ምስል መስገድ"Icon veneration" በኦርቶዶክስ እና በካቶሊክ ክርስትና እሙን እና ቅቡል የሆነ ትምህርት ነው። እኛም ሙሥሊሞች ደግሞ ለእናንተ የምንለው ትልቅ ቁም ነገር "የፈጠራችሁን "እኔን ብቻ አምልኩኝ" ያለውን አሏህን ብቻ በብቸኝነት አምልኩ" ማለትን ነው፦
29፥56 እናንተ ያመናችሁ ባሮቼ ሆይ! ምድሬ በእርግጥ ሰፊ ናት፥ ብትቸገሩ ተሰደዱ። "እኔን ብቻ አምልኩኝ"፡፡ يَا عِبَادِيَ الَّذِينَ آمَنُوا إِنَّ أَرْضِي وَاسِعَةٌ فَإِيَّايَ فَاعْبُدُونِ
11፥2 እንዲህ በላቸው፡- «አሏህን እንጂ ሌላን አታምልኩ! እኔ ለእናንተ ከእርሱ የተላክሁ አስጠንቃቂ እና አብሳሪ ነኝ»። أَلَّا تَعْبُدُوا إِلَّا اللَّهَ ۚ إِنَّنِي لَكُم مِّنْهُ نَذِيرٌ وَبَشِيرٌ

የፈጠረንን አንዱን አምላክ ብቻ ማምለክ ምንኛ መታደል ነው? አሏህ ሂዳያህ ይስጣችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይስጠን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
August 20, 2026 15.1K 1 49