አሏህ አምሳያ የለውም
በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
16፥74 ለአሏህ አምሳያዎችን አታድርጉ፡፡ فَلَا تَضْرِبُوا لِلَّهِ الْأَمْثَالَ
አምላካችን አሏህ የሰማያት እና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነው፥ ለእርሱ ሞክሼ የለውም፦
19፥65 እርሱ የሰማያት እና የምድር በሁለቱም መካከል ላለው ሁሉ ጌታ ነውና አምልከው! እርሱን በአምልኮቱ ላይ ታገስ፡፡ ለእርሱ ሞክሼን ታውቃለህን? رَّبُّ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضِ وَمَا بَيْنَهُمَا فَاعْبُدْهُ وَاصْطَبِرْ لِعِبَادَتِهِ ۚ هَلْ تَعْلَمُ لَهُ سَمِيًّا
"ሠሚይ" سَمِيّ ማለት "ሞክሼ" ማለት ሲሆን አምላካችን አሏህ ከፍጥረት የሚመስለው ምንም ነገር የለም፦
42፥11 የሚመስለው ምንም ነገር የለም፡፡ እርሱም ሰሚው ተመልካቹ ነው፡፡ لَيْسَ كَمِثْلِهِ شَيْءٌ ۖ وَهُوَ السَّمِيعُ الْبَصِيرُ
እዚህ አንቀጽ ላይ "ሚስሊ" مِثْلِ የሚለው የግሥ መደብ ነው፥ "ሚስል" مِثْل ወይም "ሚሳል" مِثَال የስም መደብ ሲሆን "አምሳያ" "ምሳሌ" ማለት ነው። ለአሏህ ምንም ዓይነት አምሳል የለውም፥ ለእርሱ አንድም ብጤ የለውም፦
114፥4 «ለእርሱም አንድም ብጤ የለውም»። وَلَمْ يَكُن لَّهُ كُفُوًا أَحَدٌ
"ኩፉው" كُفُو ማለት "ወደር" "እኩያ" "አቻ" "ቢጤ" "አምሳያ" "ተፎካካሪ" "ባላንጣ" ማለት ሲሆን እርሱ የሚተካከለው አቻ እና እኩያ እንዲሁ የሚመሳሰለው አምሳያ እና ቢጤ የለውም። በዲኑል ኢሥላም ለአሏህ አምሳያዎችን ማድረግ ሺርክ ነው፦
16፥74 ለአሏህ አምሳያዎችን አታድርጉ፡፡ فَلَا تَضْرِبُوا لِلَّهِ الْأَمْثَالَ
እዚህ አንቀጽ ላይ "አምሳያዎች" ለሚለው የገባው ቃል "አምሳል" أَمْثَال ሲሆን "ሚስል" مِثْل ወይም "ሚሳል" مِثَال ለሚለው ብዙ ቁጥር ነው፥ ስለዚህ አሏህ ምሳሌ ወይም አምሳል የለውምና አከሌ "በአሏህ አምሳል ወይም ምሳሌ ተፈጠረ" የሚል ትምህርት በዲናችን የለም።
በባይብል ግን ሰው የተፈጠረው በአምላክ ምሳሌ ወይም አምሳል እንደሆነ ይናገራል፦
ዘፍጥረት 1፥26 አምላክም፦ “ሰውን በመልካችን እና እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር" አለ። וַיֹּאמֶר אֱלֹהִים נַעֲשֶׂה אָדָם בְּצַלְמֵנוּ כִּדְמוּתֵנוּ
ልብ ብላችሁ እንደሆነ "መልክ" ለሚለው የገባው ቃል "ጼሌም" צֶלֶם " ሲሆን "ምሳሌ" ለሚለው የገባው ቃል "ድሙት" דְּמוּת ነው፥ በግሪክ ሰፕቱአጀንት "መልክ" ለሚለው የገባው ቃል "ኤይኮን" εἰκών ሲሆን "ምሳሌ" ለሚለው የገባው ቃል ደግሞ "ሆሞዮሲስ" ὁμοίωσις ነው፦
ዘፍጥረት 1፥26 አምላክም፦ “ሰውን በመልካችን እና እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር" አለ። καὶ εἶπεν ὁ Θεός· ποιήσωμεν ἄνθρωπον κατ᾿ εἰκόνα ἡμετέραν καὶ καθ᾿ ὁμοίωσιν,
በዐረቢኛው ባይብል ላይ "መልክ" ለሚለው የገባው ቃል "ሱራህ" صُورَة ሲሆን "ምሳሌ" ለሚለው የገባው ቃል ግን "ሚሳል" مِثَال ነው፦
ዘፍጥረት 1፥26 አሏህም፦ “ሰውን በመልካችን እና እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር" አለ። ثُمَّ قَالَ اللهُ: «لِنَخلِقِ النَّاسَ عَلَى صُورَتِنَا وَكَمِثَالِنَا
"አምሳል" የግዕዝ ቃል ሲሆን "ምሳሌ"Similar" ማለት ነው። "አሏህ አደምን በመልኩ ፈጠረ" የሚል ሐዲስ ላይ አለ፥ በዚህ ነጥብ ላይ ከዚህ ቀደም የጦመርነው መጣጥፍ ስላለ ይመልከቱ፦ https://t.me/Wahidcom/4073
ነገር ግን "ሰው በአሏህ አምሳል" ተፈጠረ የሚል አስተምህሮት በዲናችን የለም፥ ምክንያቱም አሏህ አምሳያ የለውም። በተጨማሪ፦
ያዕቆብ 3፥9 በእርሱም(በአንደበት) እንደ አምላክ "ምሳሌ" የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። καὶ ἐν αὐτῇ καταρώμεθα τοὺς ἀνθρώπους τοὺς καθ’ ὁμοίωσιν Θεοῦ γεγονότας·
እዚህ አንቀጽ ላይ "ምሳሌ" ለሚለው የገባው ቃል ደግሞ "ሆሞዮሲስ" ὁμοίωσις እንደሆነ ልብ አድርግ! አንዲት ሙሥሊም እኅታችን ባለማወቅ ስለ ሰው "አሏህ በአምሳሉ የፈጠረውን ፍጡር" ብላ ስትናገር ሙሥሊሞች "አሏህ አምሳያ የለውም፥ አሏህ ሰውን በአምሳሉ ፈጠረ" የሚል ትምህርት ባይብል ላይ እንጂ ቁርኣን ላይ ወይም ሐዲስ ላይ የለም" ሲሉ ዐላዋቂ ክርስቲያኖች ደግሞ "አሏህ አደምን በመልኩ ፈጠረ" የሚለውን ሐዲስ ያለ ቦታው እና ዐውዱ ጠቅሰዋል። ቅሉ እና ጥቅሉ ግን "መልክ" ማለት እና "ምሳሌ" ማለት ይለያያል፥ አሁንም ቢሆን "አሏህ ሰውን በአምሳሉ ፈጠረ" የሚል ትምህርት ቁርኣን እና ሐዲስ ላይ የለም።
"አሏህ ሰውን በአምሳሉ ፈጠረ" የሚል ሙግት ሥነ አምክኖአዊ ሕፀፅ"Logical fallacy" አለበት፥ የሙግቱ ድምዳሜ በማስረጃ አልባ ስለተደመደመ ከመረጃ አልባ የመጣ ሕፀፅ"Argument from silence fallacy" ከመሆን ባሻገር በማንለው እና በማናምንበት ሙግት ዐዋቅሮ እና አደራጅቶ መሞገት ቁልመማዊ ሕፀፅ"Straw man fallacy" ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይወፍቃችሁ! እኛንም ኢሥቲቃማህ ይወፍቀን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም
August 31, 2026 4.1K 4 12