ፍዝዝ፣ ድንግዝ እና ድንዝዝ ብላችሁ መውቀሱን እና መክሰሱን ትታችሁ በእናንተ መጽሐፍ ያለውን ይህንን ነጥብ ተመልከቱ! አምላክ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ እና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ ይፈልጋል፦
1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥4 እርሱ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ እና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ "ይፈልጋል"። ὃς πάντας ἀνθρώπους θέλει σωθῆναι καὶ εἰς ἐπίγνωσιν ἀληθείας ἐλθεῖν.
በአዲሱ መደበኛ ትርጉም "ይፈልጋል" ለሚለው የገባው ቃል "ቴሌይ" θέλει ሲሆን ሥርወ ቃሉ "ቴሎ" θέλω ነው፥ "ቴሌማ" θέλημά ማለት "ፈቃድ"will" ማለት ሲሆን ቴሌማ እራሱ "ቴሌማ አፖዶሲስ" θέλημά ἀπόδοσις እና "ቴሌማ ፕሮታሲስ" θέλημά πρότᾰσῐς ተብሎ ለሁለት ይከፈላል። "ቴሌማ አፖዶሲስ" θέλημά ἀπόδοσις ማለት "ቀዳማይ ፈቃድ" ማለት ሲሆን ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ እና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ የአምላክ ቀዳማይ ፈቃድ ነው፥ "ቴሌማ ፕሮታሲስ" θέλημά πρότᾰσῐς ማለት "ደኃራይ ፈቃድ" ማለት ሲሆን ሰዎች ካመፁ ለገሃነም መሆናቸው የአምላክ ደኃራይ ፈቃድ ነው። ዮሐንስ ዘደማስቆ"John of Damascus" ይህንን ነጥብ አፋፍቶ እና አዳብሮ አስቀምጦታል፦
"እንዲሁም የአምላክ የመጀመሪያ ፍላጎት ሁሉም ሰው እንዲድን እና ወደ መንግሥቱ እንዲመጣ መሆኑን ማስታወስ አለብን! 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥4 እርሱ ቸር አምላክ ስለሆነ ከቸርነቱ እንድንካፈል እንጂ ለቅጣት አላዘጋጀንም፥ ነገር ግን እርሱ ፍትሓዊ አምላክ ስለሆነ ኃጢአተኞች ቅጣት እንዲደርስባቸው ፈቃዱ ነው። የመጀመሪያው የአምላክ ቀዳማይ ፈቃድ እና ደስታ፣ ከእርሱ የመነጨ፣ ተብሎ ይጠራል፥ ሁለተኛው ደግሞ የአምላክ ደኃራይ ፈቃድ እና ፍላጎት፣ መነሻው በእኛ ውስጥ ተብሎ ይጠራል"።
Exposition of the Orthodox Faith (John of Damascus) Book II(2) chapter 29
ዮሐንስ ዘደማስቆ ይህንን ያብራራው 1ኛ ጢሞቴዎስ 2፥4 ያለውን ዐውድ በተናገረበት ነው። ዮሐንስ አፈ ወርቅ"John Chrysostom" ይህንን ነጥብ አበጥሮ እና አንጠርጥሮ ፊት የማያስመልስ አገንት የማያስቀልስ አድርጎ አስቀምጦታል፦
"ይህ ማለት ግን እርሱ ከምሩ ስለፈቀደ ነው፥ ይህ አንድ ኃያል እንደሚለው የእርሱ ምራዊ ፍላጎት ነው። መልካም ደስታ የሚለው ቃል በሁሉም ቦታ ማለት ቀዳማይ ፈቃድ ማለት ነው፥ ምክንያቱም ሌላ ፈቃድም አለ። ለምሳሌ፦ የመጀመሪያው ፈቃድ ኃጢአተኞች እንዳይጠፉ ነው፥ ሁለተኛው ፈቃድ ሰዎች ክፉ ከሆኑ እንዲጠፉ ነው"።
Homilies on Ephesians (Chrysostom) Homily 1 Ephesians 1፥5
እንግዲህ እነዚህን አበው ከተቀበላችሁ በቁርኣን የተቀመጠውን የአሏህን ፈቃድ ውልግድ እና ውልብድ፣ ወለም እና ዘለም፣ ውልፍጥ እና ዝልፍጥ ሳትሉ በቅጡ እና በአግባብ መረዳት ትችላላችሁ። አምላካችን አሏህ ሂዳያውን ይወፍቃችሁ! ለእኛም ኢሥቲቃማውን ይወፍቀን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም
August 16, 2026 15.9K 1 30