የአሏህ ፈቃድ በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው። 81፥29 የዓለማቱ ጌታ አሏህ… — ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics" — TG.ME

የአሏህ ፈቃድ

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።

81፥29 የዓለማቱ ጌታ አሏህ ካልፈቀደ አትፈቅዱም፡፡ وَمَا تَشَاءُونَ إِلَّا أَن يَشَاءَ اللَّهُ رَبُّ الْعَالَمِينَ

"መሺኣህ" مَشِئَة የሚለው ቃል "ሻአ" شَاءَ ማለትም "ፈቀደ" ከሚለው ሥርወ ቃል የመጣ ሲሆን "ፈቃድ"Will" ማለት ነው፥ የአሏህ ፈቃድ "መሺኣህ ሙቀደማህ" مَشِئَة مُقَدِّمَة እና "መሺኣህ ነቲጃህ" مَشِئَة نَتِيجَة ተብሎ ለሁለት ይከፈላል።
፨ "ሙቀደማህ" مُقَدِّمَة ማለት "ቀዳማይ"Antecedent" ማለት ሲሆን "መሺኣህ ሙቀደማህ" مَشِئَة مُقَدِّمَة ማለት "ቀደማይ ፈቃድ"Antecedent Will" ማለት ነው፥ አምላካችን አሏህ ለዓለማት በደልን የሚሻ አይደለም፡፡ ለባሪያዎቹ ከህደትን አይወድም፦
3፥108 አሏህ ለዓለማት በደልን የሚሻ አይደለም፡፡ وَمَا اللَّهُ يُرِيدُ ظُلْمًا لِّلْعَالَمِينَ
23፥31 አሏህ ለባሮቹ በደልን የሚሻ አይደለም፡፡ وَمَا اللَّهُ يُرِيدُ ظُلْمًا لِّلْعِبَادِ

ሰዎች ቢክዱ አሏህ ከከሓዲዎች የተብቃቃ ነው፥ ለባሪያዎቹም ከህደትን አይወድም። ብናምን ግን እርሱን ይወድልናል፦
39፥7 ብትክዱ አሏህ ከእናንተ የተብቃቃ ነው፥ ለባሪያዎቹም ከህደትን አይወድም። ብታመሰግኑ እርሱን ይወድላችኋል፡፡ إِن تَكْفُرُوا فَإِنَّ اللَّهَ غَنِيٌّ عَنكُمْ ۖ وَلَا يَرْضَىٰ لِعِبَادِهِ الْكُفْرَ ۖ وَإِن تَشْكُرُوا يَرْضَهُ لَكُمْ

አሏህ ቸር እና ደግ ስለሆነ በሰዎች ገሩን ነገር መሻቱ እና በሰዎች ችግሩን አለመሻቱ የእርሱ ቀደማይ ፈቃድ ነው፦
2፥185 አሏህ በእናንተ ገሩን ነገር ይሻል፥ በእናንተም ችግሩን አይሻም፡፡ يُرِيدُ اللَّهُ بِكُمُ الْيُسْرَ وَلَا يُرِيدُ بِكُمُ الْعُسْرَ

፨ "ነቲጃህ" نَتِيجَة ማለት "ደኃራይ"Consequent" ማለት ሲሆን "መሺኣህ ነቲጃህ" مَشِئَة نَتِيجَة ማለት "ደኃራይ ፈቃድ"Consequent Will" ማለት ነው፥ አምላካችን አሏህ ለሰው የሰጠውን ፈቃድ በአሏህ ደኃራይ ፈቃድ ሥር ነው፦
81፥29 የዓለማቱ ጌታ አሏህ ካልፈቀደ አትፈቅዱም፡፡ وَمَا تَشَاءُونَ إِلَّا أَن يَشَاءَ اللَّهُ رَبُّ الْعَالَمِينَ

አሏህ በደኃራይ ፈቃዱ ለሰው ነጻ ፈቃድ ስለሰጠው ሰው የማመን እና የመካድ ፈቃድ አለው፦
18፥29 «እውነቱም ከጌታችሁ ነው፡፡ የፈቀደ ሰው ይመን፤ የፈቀደ ሰው ይካድ» በላቸው፡፡ وَقُلِ الْحَقُّ مِن رَّبِّكُمْ ۖ فَمَن شَاءَ فَلْيُؤْمِن وَمَن شَاءَ فَلْيَكْفُر

"የፈቀደ" ለሚለው የግሥ መደብ የገባው ቃል "ሻአ" شَاءَ ሲሆን ሰው ኸይር እና ሸር የሆኑ ሁለት አማራጭ መምረጥ የሚችል ፍጡር መሆኑን በቂ ማሳያ ነው፦
72፥14 የሠለሙ ሰዎች እነዚያ ቅንን መንገድ መረጡ፡፡ فَمَنْ أَسْلَمَ فَأُولَـٰئِكَ تَحَرَّوْا رَشَدًا
41፥17 ሰሙዶችማ መራናቸው ዕውርነትንም በቅንነት ላይ መረጡ፡፡ وَأَمَّا ثَمُودُ فَهَدَيْنَاهُمْ فَاسْتَحَبُّوا الْعَمَىٰ عَلَى الْهُدَىٰ

አሏህ ቢሻ ኖሮ በምድር ያሉት ሰዎች ሁሉ አማኝ ያረግ ነበር፥ በተቃራኒው አሏህ ቢሻ ኖሮ ከሓድያንን ባላጋሩ ነበር፦
10፥99 ጌታህም ቢሻ ኖሮ በምድር ያሉት ሰዎች ሁሉም የተሰበሰቡ ሆነው ባመኑ ነበር፡፡ ታዲያ አንተ ሰዎችን አማኞች እንዲኾኑ ታስገድዳለህን?። وَلَوْ شَآءَ رَبُّكَ لَـَٔامَنَ مَن فِى ٱلْأَرْضِ كُلُّهُمْ جَمِيعًا ۚ أَفَأَنتَ تُكْرِهُ ٱلنَّاسَ حَتَّىٰ يَكُونُوا۟ مُؤْمِنِينَ
6፥107 አሏህ ቢሻ ኖሮ ባላጋሩ ነበር፥ በእነርሱ ላይ ጠባቂ አላደረግንህም፡፡ አንተ በእነርሱ ላይ ኃላፊ አይደለህም፡፡ وَلَوْ شَاءَ اللَّهُ مَا أَشْرَكُوا ۗ وَمَا جَعَلْنَاكَ عَلَيْهِمْ حَفِيظًا ۖ وَمَا أَنتَ عَلَيْهِم بِوَكِيلٍ

አሏህ በቀዳማይ ፈቃዱ ሁሉንም አማኝ ቢያደርግ ማስገደድ ስለሆነ ከነጻ ፈቃድ ጋር ይጻረር ነበር፥ በተቃራኒው በቀዳማይ ፈቃዱ ከሓዲያን እንዳይክዱ ቢያደርግ ማስገደድ ስለሆነ ከግብረገባዊ ተጠያቂነት ጋር ይጻረር ነበር። ሰዎች በነጻ ፈቃዳቸው እንዲያምኑ መፍቀዱ እና በነጻ ፈቃዳቸው እንዲክዱ መፈቀዱ ደኃራይ ፈቃዱ ነው፥ አማንያን ወደ ጀነት የሚገቡት በእምነታቸው ምክንያት እና ይሠሩት በነበሩት ምክንያት ነው፦
10፥9 እነዚያ ያመኑ እና መልካም ሥራዎችን የሠሩ ጌታቸው "በእምነታቸው ምክንያት" የገነትን መንገድ ይመራቸዋል፥ ከሥራቸው ወንዞች ይፈስሳሉ፡፡ በመጠቀሚያ ገነቶች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ إِنَّ الَّذِينَ آمَنُوا وَعَمِلُوا الصَّالِحَاتِ يَهْدِيهِمْ رَبُّهُم بِإِيمَانِهِمْ ۖ تَجْرِي مِن تَحْتِهِمُ الْأَنْهَارُ فِي جَنَّاتِ النَّعِيمِ
46፥14 እነዚያ የገነት ጓዶች ናቸው፡፡ በእርሷ ውስጥ ዘውታሪዎች ሲኾኑ፡፡ በዚያ "ይሠሩት በነበሩት ምክንያት" ታላቅን ምንዳ ይመነዳሉ፡፡ أُولَـٰئِكَ أَصْحَابُ الْجَنَّةِ خَالِدِينَ فِيهَا جَزَاءً بِمَا كَانُوا يَعْمَلُونَ

"በእምነታቸው ምክንያት" "ይሠሩት በነበሩት ምክንያት" የሚለው ይሰመርበት! በተቃራኒው ከሓዲያን ወደ ጀሀነም የሚገቡት በክህደታቸው ምክንያት እና ይሠሩት በነበሩት ምክንያት ነው፦
6፥30 «ትክዱት በነበራችሁት "ምክንያት" ቅጣቱን ቅመሱ» ይላቸዋል፡፡ قَالَ فَذُوقُوا الْعَذَابَ بِمَا كُنتُمْ تَكْفُرُونَ
10፥8 እነዚያ "ይሠሩት በነበሩት "ምክንያት" መኖሪያቸው በእሳት ውስጥ ነው፡፡ أُولَـٰئِكَ مَأْوَاهُمُ النَّارُ بِمَا كَانُوا يَكْسِبُونَ

"ትክዱት በነበራችሁት ምክንያት" "ይሠሩት በነበሩት ምክንያት" የሚለው ይሰመርበት! ስለዚህ የአሏህ ቀደማይ ፈቃድ ሰው ከጀሀነም እንዲድን ነው፥ ነገር ግን አሏህ ፈራጅ እና ፍትኸኛ ስለሆነ ሰው በምርጫው የጀሀነም መሆን ምርጫው ካረገ እንዲቀጣ መፍቀዱ የአሏህ ደኃራይ ፈቃዱ ነው።
August 16, 2026 12.6K 26