ኢየሱስ መንገድ ነው!
በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
5፥75 የመርየም ልጅ አልመሢሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ مَّا الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ
ኢየሱስ ወደ ጌታ አምላክ የሚያደርስ መንገድ ስለሆነ ለፊልጶስ፦ "የእውነት እና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ" አለው፦
ዮሐንስ 14፥6 ኢየሱስም እንዲህ አለው፦ "የእውነት እና የሕይወት መንገድ እኔ ነኝ፥ በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም"።(የ 2000 ዕትም 80 አሓዱ)
ግዕዙም በተመሳሳይ፦ "አነ ውእቱ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት" እንደሚለው ተመልከት! "መንገድ" ማለት በመነሻ እና በመዳረሻ መካከል ያለ "መካከለኛ"Mediator" ነው፥ ካለ መካከለኛ መልእክተኛ በኩል ወደ ጌታ አምላክ መድረስ አይቻልም፦
1 ጢሞቴዎስ 1፥5 አንድ አምላክ አለና፥ በአምላክ እና በሰዎች መካከል ያለው "መካከለኛው" ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። εἷς γὰρ Θεός, εἷς καὶ μεσίτης Θεοῦ καὶ ἀνθρώπων, ἄνθρωπος Χριστὸς Ἰησοῦς,
ይህ ጥቅስ በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ "መካከለኛ" የተባለው ከአንዱ አምላክ ውጪ "ሰው" እንደሆነ ይናገራል፥ እዚህ አንቀጽ ላይ "መካከለኛ" ለሚለው የገባው ቃል "ሜሲተስ" μεσίτης ነው። ሙሴ ከኢየሱስ መላክ በፊት በብሉይ ኪዳን በአምላክ እና በሕዝቡ መካከል ሆኖ መልእክት ሲያስተላልፍ የነበረ መካከለኛ ነበረ፦
ዘዳግም 5፥5 እኔ የያህዌህን ቃል እነግራችሁ ዘንድ በዚያን ጊዜ በያህዌህ እና በእናንተ መካከል ቆሜ ነበር።
"በያህዌህ እና በእናንተ መካከል" የሚለው ኃይለ ቃል ይሰመርበት! ሙሴ ተስፋው የተሰጠው ዘር መሢሑ እስኪመጣ "መካከለኛ" ነበረ፦
ገላትያ 3፥19 ሕጉ የመጣው በመላእክት በኩል በአንድ "መካከለኛ እጅ" ነበር።(አዲሱ መደበኛ ትርጉም) διαταγεὶς δι’ ἀγγέλων ἐν χειρὶ μεσίτου.
ሕግ የመጣው በመላእክት በኩል ነው፥ በተለይ "በስተ ቀኙም የእሳት ሕግ ነበረላቸው" የሚለውን ስንረዳ የእሳት ሕግ የተባለው ቶራህ ሲሆን ቅዱሳኑ የተባሉት መላእክት ናቸው። ዘዳግም 33፥2 የሐዋርያት ሥራ 7፥53 ዕብራውያን 2፥2 ተመልከት!
ገላትያ 3፥19 "መካከለኛ" ለሚለው የገባው ቃል "ሜሲቶዩ" μεσίτου ሲሆን "እጅ" የሚለውን ለማገናዘብ የመጣ አገናዛቢ ነው፥ ይህም "መካከለኛ" የሚለው ቃል "ሙሴ" የሚለውን ስም ተክቶ የመጣ ነው። ዘኍልቍ 4፥37 ነህምያ 9፥14 ነህምያ 10፥29 ነህምያ 8፥15 ተመልከት!
"በመካከለኛ እጅ" የሚለው "በሙሴ እጅ" የሚለውን ለመተካት የመጣ እንደሆነ ካየን ዘንዳ ሙሴ "መካከለኛ" መባሉ አስረግጠን እና ረግጠን መናገር እንችላለን። መካከለኛው ሙሴ መካከለኛነቱ ለአንድ ማንነት ሳይሆን ለአዛዥ አምላክ እና ለታዛዥ ሕዝቡ ሲሆን አምላክ ግን አንድ ማንነት ነው፦
ገላትያ 3፥20 መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም፥ አምላክ ግን አንድ ነው። ὁ δὲ μεσίτης ἑνὸς οὐκ ἔστιν, ὁ δὲ Θεὸς εἷς ἐστιν.
ኢዮብ 9፥32 እጁን በሁለታችን ላይ የሚያኖር "መካከለኛ" በመካከላችን ምነው በተገኘ። εἴθε ἦν ὁ μεσίτης ἡμῶν καὶ ἐλέγχων καὶ διακούων ἀνὰ μέσον ἀμφοτέρων·
ኢዮብ ከሙሴ በፊት በእርሱ እና በአምላኩ መካከል "መካከለኛ" እንዲኖር ተመኝቶ ከ 400 ዓመት በኃላ ሙሴ መካከለኛ ሆኖ ተነስቷል። ታዲያ ሙሴ ምን ነበር? ሰው እና ነቢይ ወይስ የአምላክ እና የሰው ውሕደት? "መካከለኛ" ማለት "የአምላክ እና የሰው ውሕደት" ነው" ብለው የሚቀጥፉ ሰዎች ሙሴ "መካከለኛ" መባሉን ሲረዱ ምን ይውጣቸው ይሆን? ኢየሱስም በአዲስ ኪዳን "መካከለኛ" የተባለው ሙሴ በተባለበት ቀመር እና ሒሣብ ነው፥ ይህም ሰው በአምላክ እና በሕዝቡ መካከል በሥራ እና በቃል ብርቱ ነቢይ የነበረው የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው። የናዝሬቱ ኢየሱስ ከአምላክ እየሰማ ለሕዝቡ የሚናገር መካከለኛ ሰው ነበር፦
ሉቃስ 24፥19 በአምላክ እና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራ እና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ።
ዮሐንስ 8፥40 ነገር ግን አሁን ከአምላክ የሰማሁትን እውነት የነገርኋችሁን ሰው ልትገድሉኝ ትፈልጋላችሁ?።
አምላክ ባለቤት ሲሆን ሰው ተሳቢ ነው፥ በባለቤት እና በተሳቢ መካከል "የሰማሁት" የሚል አጫፋሪ ግሥ አለ፥ ይህ ቁልጭ እና ፍንትው አድርጎ የሚያሳየው በላከው አምላክ እና በተላከው መካከለኛ ሰው ያለውን የማንነት እና የምንነት ልዩነት ነው። ስለዚህ በአምላክ እና በሰዎች መካከል መካከለኛ መንገድ ነቢይ እና መልእክተኛ ነው፥ ወደ አምላክ የሚያደርስ ነቢይ እንጂ አምላክ የለም። እርግጥ ነው! ኢየሱስ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም፦
5፥75 የመርየም ልጅ አልመሢሕ ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ مَّا الْمَسِيحُ ابْنُ مَرْيَمَ إِلَّا رَسُولٌ قَدْ خَلَتْ مِن قَبْلِهِ الرُّسُلُ
አምላካችን አሏህ በእርሱ መንገድ ከሚጓዙ ባሮቹ ያርገን! ከጥመት መንገድ ይጠብቀን! አሚን።
✍ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom
ወሠላሙ ዐለይኩም
August 15, 2026 12.8K 1 49