የአምልኮ መገዛት በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡ 3፥51 «አሏህ ጌታዬ እና… — ወሒድ የዕቅበተ ኢሥላም መጣጥፍት"Wahid Articles of Islamic Apologetics" — TG.ME

የአምልኮ መገዛት

በአሏህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው፡፡

3፥51 «አሏህ ጌታዬ እና ጌታችሁ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» አላቸው፡፡ إِنَّ اللَّهَ رَبِّي وَرَبُّكُمْ فَاعْبُدُوهُ ۗ هَـٰذَا صِرَاطٌ مُّسْتَقِيمٌ

"የባሕርይ መገዛዛት"Ontological subordination" ማለት በባሕርይ የማይመሳሰሉ ሆነው ነገር ግን በባሕርይ አንዱ ከሌላው ስለሚበልጥ በመካከላቸው ገዥ እና ተገዥ አለ። ለምሳሌ፦ ሰው እና እንስሳ በምንነት የተለያዩ "ባሕርይ"Essence" ስላላቸው ሰው ገዥ እንስሳ ተገዥ ነው፦
መዝሙር 8፥6 ሁሉን ከእግሮቹ በታች አስገዛህለት። πάντα ὑπέταξας ὑποκάτω τῶν ποδῶν αὐτοῦ,

እዚህ አንቀጽ ላይ ለመገዛት የገባው ሥርወ ቃል "ሃይፖታሶ" ὑποτάσσω ሲሆን ገዥው ሰው ተገዥው በጎችን፣ ላሞችን፣ ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፣ የሰማይንም ወፎች፣ የባሕርን ዓሦች፣ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ ነው፦
ዘፍጥረት 1፥28 የባሕርን ዓሦችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ "ግዙአቸው"።
መዝሙር 8፥8 በጎችን፣ ላሞችን፣ ሁሉ ደግሞም የምድረ በዳውን እንስሶች፣ የሰማይንም ወፎች፣ የባሕርን ዓሦች፣ በባሕር መንገድ የሚሄደውንም ሁሉ።

እንስሳ ሰውን የሚገዛው የባሕርይ ቢሆንም የአክብሮት መገዛት እንጂ የአምልኮ መገዛት አይደለም። ነገር ግን ኢየሱስ ፍጡር ስለሆነ ለአምላክ የሚገዛበትን ለማሳየት የገባው ሥርወ ቃል "ሃይፖታሶ" ὑποτάσσω ነው፦
1ኛ ቆሮንቶስ 15፥28 ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን "አምላክ" ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት "ይገዛል"። ὅταν δὲ ὑποταγῇ αὐτῷ τὰ πάντα, τότε καὶ αὐτὸς ὁ Υἱὸς ὑποταγήσεται τῷ ὑποτάξαντι αὐτῷ τὰ πάντα, ἵνα ᾖ ὁ Θεὸς πάντα ἐν πᾶσιν.

"ሆ ቴዎስ" ማለት "አምላክ" ማለት ሲሆን ኢየሱስ ሁሉን ላስገዛለት አምላክ ይገዛል፥ ለአምላክ የሚደረግ መገዛት የባሕርይ መገዛት ሲሆን የአምልኮ መገዛት ነው፦
ያዕቆብ 4፥7 እንግዲህ ለአምላክ "ተገዙ"! ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል። ὑποτάγητε οὖν τῷ Θεῷ· ἀντίστητε δὲ τῷ διαβόλῳ, καὶ φεύξεται ἀφ’ ὑμῶν·

እዚህ አንቀጽ ላይ "ተገዙ" ለሚለው የገባው ቃል በተመሳሳይ "ሃይፖታሶ" ὑποτάσσω ነው፥ ስለዚህ ኢየሱስ በምንነት ሰው፣ የሰው ልጅ፣ ፍጡር በማንነቱ ነቢይ፣ መልእክተኛ እና መሢሕ ስለሆነ ለአምላኩ የሚገዛው መገዛት የአምልኮ መገዛት ነው። ኢየሱስ በምድራዊ ቆይታው አምላኩን ሲለምን፣ ሲጸልይ፣ ሲሰግድለት፣ ሲጦም እና ሲፈራው ከማየት ባሻገር አሁን ላይ ሰማይ የአምላኩ አገልጋይ ነው፦
ዕብራውያን 8፥2 እርሱ በመቅደስ "አገልጋይ" ነው። τῶν ἁγίων λειτουργὸς

እዚህ አንቀጽ ላይ "ሌይቶሬዎርጎስ" λειτουργός ሲሆን የግሥ መደቡ "ላትሬኦ" λατρεύω ነው፥ "ላትሬያ" λατρεία ማለት "አምልኮ" ማለት ሲሆን ኢየሱስ በሰማይ ባለው መቅደስ "አምላኪ"(አገልጋይ) ሰለሆነ ሰማይ ላይ "አምላካችን" እያለ የሚናገርለት አምላክ አለው፦
ራእይ 19፥5 ድምፅም እንዲህ ሲል ከዙፋኑ ወጣ፦ “ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ! "አምላካችንን" አመስግኑ”። καὶ φωνὴ ἀπὸ τοῦ θρόνου ἐξῆλθεν λέγουσα Αἰνεῖτε τῷ Θεῷ ἡμῶν, πάντες οἱ δοῦλοι αὐτοῦ, οἱ φοβούμενοι αὐτόν, οἱ μικροὶ καὶ οἱ μεγάλοι.

"አምላካችን" የሚለው ቃል ይሰመርበት! ከዙፋኑ የወጣው "አምላካችን" የሚል ድምፅ በዙፋኑ መካከል ካለው ከኢየሱስ የወጣ ድምፅ ነው፥ "በዚያን ጊዜ" ማለት በሚመጣበት ጊዜ ንግሥና እና መገዛት ለሰው መሆኑ ቀርቶ አምላኩ ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ ኢየሱስ ለአምላኩ የአምልኮ መገዛት በግልጽ እና በይፋ ይገዛል። የእርሱ አስተምህሮት «አሏህ ጌታዬ እና ጌታችሁ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» የሚል ነው፦
3፥51 «አሏህ ጌታዬ እና ጌታችሁ ነው፥ ስለዚህ አምልኩት! ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው» አላቸው፡፡ إِنَّ اللَّهَ رَبِّي وَرَبُّكُمْ فَاعْبُدُوهُ ۗ هَـٰذَا صِرَاطٌ مُّسْتَقِيمٌ

ክርስቲያኖች ሆይ! ኢየሱስ ያመለከውን አምላክ እንድታመልኩ ጥሪያችን ነው። አምላካችን አሏህ ሂዳያህ ይወፍቃችሁ! ለእኛም ጽናቱን ይወፍቀን! አሚን።

ከዐቃቢ ኢሥላም ወሒድ
https://t.me/Wahidcom

ወሠላሙ ዐለይኩም
August 12, 2026 13.6K 2 29