ትርጓሜ ዘመዝሙር / ይሁበነ ዝናመ / ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ፤ ዝናሙን ጠሉን በጊዜው ይሰጠናል በጊዜው ይስጠን… — ፀዊረ መስቀል — TG.ME

ትርጓሜ ዘመዝሙር / ይሁበነ ዝናመ /

ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ፤
ዝናሙን ጠሉን በጊዜው ይሰጠናል በጊዜው ይስጠን ዝናም ለዘር ጠል ለመከር በጊዜው ነው እና ሁሉ በጊዜው ካሌሆነ ካለጊዜው ከሆነ በዝናሙ ጊዜ ፀሐይ በፀሐዩ ጊዜ ዝናም ቢሆን ድርቅ ይመጣል ዘር በጎርፍ ያልቃል ብቃያ ይቀጠፋል እህል ከጎተራ ሳይከተት ይቀራል።


ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ
ቢያምረው ደገመው አንድም ሊቃውንት ለዜማው ማቅኛ አግብተውታል መልሶ መላልሶ መናገሩ ለዜማው መክፈያ ብቻ ሳይሆን ልመናና መልሶ መላልሶ መለመን እንደሚገባ ሲያጠይቅ ነው።

ወይሁበነ እክለ በረከት፤
ዝናሙን በጊዜ ሰጥቶ ጠሉን በጊዜው ሰጥቶ ዘሩን አበርክቶ የበረከት ፍሬ የበረከት አዝመራ ይሰጠናል።

ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ፤
እንዳለፈው

ያርኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ
ክረምቱን በወቅቱ አግብቶ ምሕረትን ያደርጋል ጌታ እንደ ሰው ልጅ ክፋት ቢሆን ዝናም ለዘር ጠል ለመከረ በነሳ ነበር እርሱ ግን እኩል ለሁሉ ዝናምን ያዘንማል  ፀሐይን ያወጣል ምሕረትን ይሰጣል ዝናም የምሕረተ እግዚአብሔር ምሳሌ ዝናም ለምድር ልምላሜን እንደሚሰጥ እግዚአብሔር በምሕረቱ እየጎበኘ የሰውን ልጅ በምድር ላይ ረጅም ዘመን ሰጥቶ ያኖረዋል።

ወይሁበነ ዝናመ በረከት፤
የበረከት ዝናምን ለሁሉ ይሰጣል ማለት ዝናሙ ቢበዛ እንደ ሰብአ ትካት ምድርን ባጠፋት የሰውን ልጆችንም ባጠፋ የተዘራውን ደምስሶ የደረሰውን አጥፍቶ ከምድር በረከትን በነሳ ነበር እርሱ ባወቀ ግን በልክ በልክ አድርጎ የበረከት ዝናምን ያዘንማል ዘርን ይሰጣል እህልን ይባርካል።

ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ
እንዳለፈው

ከሢቶ ዓይኖ ሰፊሆ የማኖ ይፌኑ ሣህሎ
ዓይኑን ከፍቶ ቀኙን ዘርግቶ ጠለ በረከት ዝናመ ክረምትን ይሰጠናል አሁን ለጌታ አይኖች መከፈት መከደነ እጆቹ መሰብሰብ መዘርጋት ኖሮበት አይደለም ወዶ ፈቅዶ መስጠቱን መናገር ነው እንጂ።

ወበዘአእመረ ይሴባሕ
እርሱ ባወቀ በዓለመ መላእከት በደቂቀ አዳም በልሳነ ፍጡራን በነባብያን አንደበት ሁሉ ይመሰገናል።

ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ
እንዳለፈው

ወሠርዓ ሰንበት ለሰብእ ዕረፍት
ዕለተ ናት ና አልፎ አልፎ ያነሳሳታል ለሰው ዕረፍተ ሥጋ ዕረፍተ ነፍስን አደለ ሰጠ።

ወብውህ ሎቱ ይኀድግ ኃጢአተ
ኃጢአትን ይቅር ዘንድ ለእርሱ የተገባ ነው ኃጢአትን ይቅር የሚል ሥልጣን የእርሱ ብቻ ነውና እንዲህ አለ ይቅር ብሎ የምሕረት ዝናምን ያድላል።

ይሁበነ ዝናመ በጊዜሁ
እንዳለፈው

ዓይነ ኩሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያሁ፤
የሁሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል

ይሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ
ሲሳየ ሥጋ እህሉን ምርቱን ሲሳየ ነፍስ በካህናት በሐዋርያት አድሮ ትምህርቱን እርሱ ራሱ ሥጋውን ደሙን ያድለናል።
August 30, 2026 111