የጌጃ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን የ70ኛ ዓመት በዓል የጋዜጣዊ መግለጫ መርሃ ግብር ተካሄደ
የጌጃ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን የምሥረታዋን 70ኛ ዓመት አስመልክቶ ያዘጋጀችው የጋዜጣዊ መግለጫ ዛሬ በጥራር ኢንተርናሽናል ሆቴል ተካሄደ። በዕለቱ ፕ/ር ብርሃኑ ቆጢሶ፣ ወንድም ታምሩ በሃጋ፣ መጋቢ ተስፋዬ ገመቹ፣ መጋቢ ዮሐንስ ሰይፉ፣ መጋቢ ደበበ ይርጋ እና እህት ርብቃ ተስፋዬ ተገኝተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ዋና ዋና ነጥቦች፦
ታሪክና ዕድገት፦ ቤተ ክርስቲያኗ ከ1948 ዓ.ም (ንጉሣዊ አገዛዝ) ጀምሮ ያለፈችበት ጉዞ በፕ/ር ብርሃኑ የቀረበ ሲሆን፣ ለታላቁ ተልእኮ ኢትዮጵያ ቢሮ በመስጠትና በመመሥረቱ ረገድ ዋና ሚና ተጫውታለች።
አገልግሎትና ቁመና፦ በአሁኑ ወቅት ከ60 በላይ አጥቢያዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅንና የእንክብካቤ ማዕከላትን በማቀፍ በ4 ክልሎች (አዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ሲዳማ) እያገለገለች ትገኛለች።
የበዓሉ መርሃ ግብሮች፦
ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም በአድዋ ድል መታሰቢያ የምስጋና ኮንፈረንስና የዶክመንተሪ ፊልም ምርቃት።
ከነሐሴ 24 - ጳጉሜ 1/2018 ዓ.ም የአምልኮ ኮንፈረንስና በመዝጊያው ቀን ከቤተ ክርስቲያኑ ግቢ የሚጀምር የወንጌል ማወጃ እግር ጉዞ።
ቀጣይ ራዕይ፦ በ2018 ዓ.ም «ወደፊት እንገስግስ!» በሚል መሪ ቃል ወንጌልን የማስፋትና አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን የመትከል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
በመጨረሻም የመርሃ ግብሩ አዘጋጆች ለመላው ምዕመናን እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች የመልካም ምኞት መልእክት አስተላልፈዋል።











