በአርባ ምንጭ ተደጋጋሚው የህገ-ወጥ ሰዎች ዝውውር፡ ጥያቄ ያስነሳው የህግ ተጠያቂነት
በአርባ ምንጭ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋሉት 32 የኤርትራ ዜጎች (14 ሴቶች፣ 11 ወንዶችና 7 ህፃናት) እንዲሁም አዘዋዋሪዎቻቸው ጉዳይ የጸጥታውን ስራ ጥረት ቢያሳይም፣ በከተማዋ ተደጋግሞ የሚታየው ይህ ህገ-ወጥ ተግባር ግን አሁንም ጥልቅ ጥያቄዎችን እያስነሳ ነው።
በሲቀላ ክፍለ ከተማ ነጭ ሳር ቀበሌ «ሲያትል አልጋ ቤት» ምድር ቤት ውስጥ ተሸሽገው የተገኙት እነዚህ ዜጎች እና ሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-23042 የሆነው አጓጓዥ ሀይሩፍ (HiRoof) ተሽከርካሪ ከአሽከርካሪው ጋር መያዙን የአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ አስታውቋል።
ሆኖም ይህ ድርጊት በአካባቢው ሲከሰት ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ጉዳዩን እጅግ አሳሳቢ ያደርገዋል። ተጠርጣሪ አሽከርካሪዎችና አዘዋዋሪዎች ጉቦ እየሰጡ ከህግ ተጠያቂነት እንደሚያመልጡ የሚነሳው ጠንካራ ቅሬታ፣ የጸጥታና የፍትህ አካላት የሚወስዱት እርምጃ ምን ያህል የማያዳግም ነው? የሚለውን አበክሮ ይጠይቃል።
የሰዎች ዝውውርን በዘላቂነት ለመግታት ተጠርጣሪዎችን ከመያዝ ባለፈ፣ በሙስና እና በህግ ክፍተቶች የሚፈጠሩ የአሰራር ብልሽቶች ላይ ጥብቅና የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። በህግ ፊት የሚደረገው ተጠያቂነት አስተማሪና ግልጽነት የተሞላበት ካልሆነ፣ በተደጋጋሚ የሚደረገው ክትትልና የጸጥታ አካላት ልፋት መና መቅረቱ አይቀርም።

11
5August 29, 2026 3.5K 1