በሬያቸውን ሸጠው ባጃጅ ውስጥ የረሱትን 60 ሺህ ብር ወዲያው አፈላልጎ ለባለቤቱ የመለሰው የባጃጁ ሹፌር
60 ሺህ ብርን በታማኝነት መመለስ — ከገንዘቡ የሚበልጥ የሰብዓዊነት ምስክር!
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በሰንበቴ ከተማ የተፈጠረው ይህ አስደናቂ ታሪክ ገንዘብ ተገኝቶ ተመለሰ ብሎ በቀላሉ የሚያልፍ አይደለም። የታማኝነት፣ የሰብዓዊነትና የመልካም ልቦና ትልቅ ምስክር ነው።
አንድ አርሶ አደር በሬ ሸጠው ከ60 ሺህ ብር በላይ የሆነ ገንዘብ ይዘው በባጃጅ ወደ ቤታቸው ሲጓዙ ገንዘቡን በባጃጁ ላይ ጥለው ወርደው ሄዱ። የባጃጁ ሹፌር አቶ አደም ደርብ ገንዘቡን ካገኙ በኋላ ለራሳቸው ሳያደርጉት፣ ባለቤቱን ለማፈላለግ ወሰኑ።
አቶ አደም ደርብ ገንዘቡን ይዘው ወደ እኔ በመምጣት ጉዳዩን በፌስቡክ ገፄ እንዳጋራላቸው ጠየቁኝ። እኔም ጉዳዩን ወዲያውኑ በማህበራዊ ሚዲያ ገፄ አጋራሁት። በአጭር ጊዜ ውስጥም በፈጣሪ እገዛ የገንዘቡን ባለቤት አቶ ሁሴን ቦና ማግኘት ቻልን፤ ገንዘቡም ወዲያውኑ ለባለቤቱ ተመለሰ።
60 ሺህ ብር ለብዙ ሰዎች ትልቅ ገንዘብ ነው። እንዲህ ያለ ገንዘብ በእጅ ሲገኝ ለራስ ጥቅም ማዋል ቀላል ሊመስል ይችላል። አቶ አደም ግን “ይህ የእኔ አይደለም” በማለት የሌላ ሰውን ንብረት ለባለቤቱ ለመመለስ ያሳዩት ቆራጥነት እጅግ የሚያስመሰግን ነው።
ይህ ተግባር የአንድን ሰው ገንዘብ ብቻ አልመለሰም፤ በሰው ላይ ያለውን እምነትም መልሷል። የገንዘቡ ባለቤት አቶ ሁሴን ቦናም ከገንዘቡ ጋር ተስፋቸውና በሰዎች ላይ ያላቸው እምነት መመለሱን ገልጸዋል።
አቶ አደም ደርብ፣ ከልብ እናመሰግናለን!
የሌላ ሰውን ንብረት እንደራስዎ ሳይቆጥሩ፣ በታማኝነትና በሰብዓዊነት ለባለቤቱ በማስረከብዎ ክብር ይገባዎታል።

24
6
4August 31, 2026 2.9K 1