መዝሙረ ተዋህዶ: post #378 — TG.ME

#እውነትም_ተለያይተናል!

አንዲት ወደ ንስሃ አባቷ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበች ተነሳሒት ሴት ወደ ንስሃ አባቷ ቀርባ ንስሃ ተቀብላ ትሄዳለች።

የንስሃ አባቷም በጣም አስተዋይ ስለነበሩ እራሳቸውን እንደ ኃጢያተኛ እያሳዩ ትህትናን ሊያስተምሯት ፈለጉ።

ልጅቷ ግን ትንሽ መጾም መጸለይ ስትጀምር በቃ ራዕይና ሕልም የማየት ምኞት ስለነበራት የሆነ ቅዠት ባጠቃት ቁጥር ሰው እየፈለገች አንዳንዴም ወደ ንስሃ አባቷ እየመጣች እሳቸውም ይሄ ቅዠት ነው ይሄ እንዲህ ሊሆን ይችላል አንቺ ግን ከዚህ አይነት ሐሳብ ውጪ እያሉ ይመክሯታል።

አንድ ቀን ግን ለየት ያለ ህልም አይታ ሕልሙንም በቁሙ ፈታችውና በደስታ ተውጣ እየተፍለቀለቀች ወደ ንስሃ አባቷ ጎምለል ጎምለል እያለች መጣች ትላንት ገና ከሩቅ ዝቅ ብላ ጉልበት ለመሳም የምትጣደፍና እጅ የምትነሳ ሽቁጥቁጥ ሴት ያ ሁሉ ትህትናዋ ጠፍቶ እንደ ንጉሥ ባለሟል ከንስሃ አባቷ ፊት እንደ ጅብራን ተገተረች።

የንስሃ አባቷም ምነው ዛሬ ምን ተገኘ ልጄ ብለው ጠየቋት
እሷም እየሳቀችና እየተጀነነች አባ በቃ ተለያየን እኮ አለቻቸው
ካህኑም በመደነቅ ምነው ልጄ ምን ተፈጠረ ይላሉ
ልጅቷም ስትመልስ በቃ አሁንማ ተለያየን ተራራቅን በቃ ምን ያልተፈጠረ ነገር አለ ትላለች
ምንድን ነው እሱ ልጄ አሏት?

እየውልዎት አባ ዛሬ ያየሁት ራዕይ ሌላ ነው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለበዓለ ንግሥ የመጣ ህዝብ ተሰብስቦ እርስዎ ማዕጠንት ይዘው ከፊት እየመሩኝ ካህናቱ እኔን ከበው አጅበውኝ መጎናጸፊያ ለብሼ ታቦት ተሸክሜ ሰው ሁሉ እልል እያለልኝ ቤተ ክርስቲያኑን ስዞር አደርኩ።
በቃ አባታችን ተለያየንኮ እንደ ቀልድ የተጀመረ ንስሐና ጸሎቴ እዚህ አደረሰኝ ብላ መለሰች።
ካህኑም ትክዝ ብለው አዎ ልጄ እውነትም ተለያይተናል ግን ያሳዝናል አሏት።

እንዴት ምኑ ነው የሚያሳዝነው?
እንዴ ታቦት ነውኮ የተሸከምሁት!

እየውልሽ ልጄ አንቺ በካህናቱ ታጅበሽ ቤተ ክርስቲያኑን መዞርሽኛ ታቦት መሸከምሽ አንቺ ሞተሽ ቤተ ክርሰቲያኑን እየዞርሽ ነው።
እኔ ደግሞ ማዕጠንት እያጠንሁ ግንዘት እየደገምሁልሽ ነው
እልል የሚለው ሕዝብ ደግሞ ለቅሶ ላይ የተገኙ ወዳጅ ዘመዶችሽ ናቸው ብለው ቢመልሱላት።

ከመደንገጧ የተነሳ እንዲያውም አባ ሕልም መተርጎም ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለውን ለማረጋገጥ እንጂ ምንም አላየሁም አለች አሉ።

እናም ይህች ሴት በአካል ታቦት የሚሸከሙ ካህናት እያሉ ገና ባልተረጋገጠ እና ፍቺው ባልታወቀ ቅዠት በህልም ታቦት ተሸከምሁ ብላ የተኩራራችው ገና ላልተረጋገጠ ህልም እራሷን ከፍ አደረገች።

ብዙዎቻችንም የዚህ ተጠቂዎች ነን ስላስቀደስን ከቀዳሾች እኩል ማኅሌት ስለቆምን መርጌቶችን ለመብለጥ ስለዘመርን ድጓ ያወቅን በስመ አብ ስላልን ትርጓሜ ያጠናቀቅን ተንሥዑ ስላልን የቅዳሴ መምህር የሆን እየመሰለን በሊቃውንቱና በእኛ መካከል ያለው አጥር ከመፍረስ አልፎ እነሱን የበለጥን እስኪመስለን ድረስ ትዕቢታችን ቅጡን ያጣብን ብዙዎች ነን።

ሙሉ ሕይወታቸውን ለቤተ ክርስቲያን የሰጡ አገልጋዮችን አንድ ሁለት ቀን በትሩፋት ስላስተማርን ስለቀደስን የስብከታችንም የንግግራችንም ማጣፈጫ እነሱን ማኮሰስ እኛን ማሞገስ የሆነብን ሰዎች አለን።

በዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን አባቶችና አገልጋዮች ላይ ያነጣጠረ ነቀፋና ትችት የበዛውኮ እንዲህ እንደዚች ሴት ወደ መንፈሳዊው አገልግሎት ቀረብ ባልን ቁጥር እራሳችንን እንደ ንፁህ እነሱን እንደ በደለኛ የማየት አባዜ ስለተጠናወተን ነውኮ።

አምላክ የትህትና ልብን ለሁላችንም ያድለን።
April 12, 2023 10K 12