+++ እምቢ +++
የሰውን ልጅ ከብዙ መከራ ሊያወጣ የሚችል መፍትሔ ነው። ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ያልተገባ ሩካቤን እና በዚያ ምክንያት የሚፈጠር ጽንስን ቀድሞ ለመከላከል የሚረዳ በቤተ ክርስቲያን የተፈቀደ ፍቱን መድኃኒት ነው። ይህን መድኃኒት ከፋርማሲ አንገዛውም ከቅጠልም አንሸመጥጠውም። እኛው ውስጥ ያለ እና ወደ አፍ የሚዋጥ ሳይሆን ከአፍ የሚወጣ መድኃኒት ነው። በእርግጥ ከአፍ የሚወጣ ቢሆንም አወጣጡ ላይ ግን ትንሽ ሊያስቸግር እና አንደበት ላይ መረር ሊል ይችላል። ያው መጎምዘዝ የብርቱ መድኃኒቶች ጠባይ ስለሆነ ይህ ብዙ አያስገርመንም። ኸረ መድኃኒቱ ይነገረን አላላችሁም? ይኸው ያዙ መድኃኒቱ "እምቢ" የሚለው አጭር ቃል ነው።
ይህ ቃል ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት የሚሆን ወሳኝ ቃል ነው። ሔዋን በእባብ ያደረ የዲያብሎስን ምክር ባትሰማ እና እምቢ ብትለው የሰው ልጅ ወደ ምድረ ፋይድ ባልወረደ ነበር። "እምቢታ" ሰይጣን እኛን ለመጥለፍ የሚያዘጋጀውን አሽክላ ቆርጠን የምንጥልበት የተሳለ ሰይፍ ነው። ጌታ በገዳመ ቆሮንቶስ ሊፈትነው የመጣን ጠላት ድል የነሣው የጠየቀውን ሁሉ ሳይቀበል ድንጋዩን ዳቦ አላደርግም፣ ወድቄ አልሰግድልህም፣ ከመቅደስም ጫፍ አልዘልም ሲል "እምቢ" በማለት ነው። ቅዱስ ያዕቆብስ "ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል" አይደል የሚለው።(ያዕቆብ 4፥7)
ለልጆቻቸው የሚሳሱና የሚጨነቁ ወላጆች ለወለዷቸው ከሚሰጧቸው ውድ ስጦታዎች አንዱ "እምቢ" ማለትን ነው። የሚሰጡበትም መንገድ ልጆቻቸው አድርጉልኝ ሲሉ የሚጠይቋቸውን አላስፈላጊ ነገሮች "እምቢ" ሲሉ በመከልከል ነው። የዛሬ ወላጆች አስፈላጊ እምቢታ የነገ የልጆች የፈተና ጊዜ መልስ ይሆናል። ዛሬ ወላጅ ሁሉን እሺ እያለ ካሳደገ፣ ነገ ልጁ ሲያድግ ክፋትና ወንጀልን "እምቢ" የሚልበት አቅም ያጣል። ለምን? ከልጅነቱ አልተማረማ።
ጲላጦስ "እምቢ" ቢል ኖሮ የአይሁድን እብደት ባገደ የንጹሑ የኢየሱስ ክርስቶስም ደም ባልፈሰሰ ነበር። እምቢ አለማለት ለክፋት እምቢታን የማያውቁ ወንበዴዎችን ያበረታታል፤ ንጹሐንን ያስፈጃል።
እስኪ ኃጢአትን፣ ክፋትን፣ ዘረኝነትን በአጠቃላይ ሰይጣንን እምቢ እንበል?
እምቢ!
ዲያቆን አቤል ካሳሁን
[email protected]
March 18, 2023 8.9K 1