«አሁን አንተ የአባትህ ልጅ ነህ? ያ አባትህ ቢያይህ እንዴት ይክፉው? ወንድ አይደለህ እንዴ ምን ያነፋርቅሃል? ልጅማ ወልዷል የሴት ወንድ፣ የአባቷ ልጅስ እሷ ናት።» ያለውን ኪዳን ሲነግረኝ ጥጋቤ አናቴ ላይ ወጥቶ አጎቴን አሳር አሳየሁት። እየሰነባበተ የሆነ ቀን አንድ የኛ መንደር ልጅ እና የአባቴ ገዳዮች ወገን ልጅ ገበያ መሃል በተነሳ የግል ፀብ ሲያያዙ መሃል ጥልቅ ብዬ <እጇ ላይ መሞቱ ነው> ብሎ ሰው ጠልቃ እስኪገባ ድረስ በጥላቻዬ ልክ ቀጠቀጥኩት። ከአጎቴ ውጪ ማንም የከፋው አልነበረም። ይባሱኑ መንደርተኛው «ቁርጥ አባቷን፣ የአባቷ ቢጤ አመፀኛ ፣ ይህቺማ የመንደሩ መድሃኒት ናት ፣ ቱ በሉ የአባቷን ደም ትመልሳለች። » እያለ ልክ እንዳደረግኩ ዓይነት በየቡናው እና ጠላ ቤቱ በወሬ ሲቀባበለኝ ባሰብኝ።
«እንደአባቴ ጫካ ካልገባሁ አልሽ!» ብሎ ሳቀ አሁንም ይሄን ሲያስታውስ «አንድ ቀን እርሻ ውዬ ስመለስ አጅሪት ለካ ያንቺ ቢጤ ወጠጤ ጎረምሶች ሰብስበሽ ሄደን ጠላቶቻችንን ካልገጠምን ብለሽ ልባቸውን ዝቅ አድርገሽ ልከሻቸው፣ ይሄ ውሻ ቢያሯሩጠው ሱሪው ላይ የሚንበጫበጭ ማቲ ሁላ <መሸፈቴ ስለሆነ ስንቅ አዘጋጁልኝ> ብሎ እናቱን ሲያውክ የሰፈሩ እናቶች ተሰብስበው ጠበቁኝ። <ይህችን ልጅ አደብ አስይዝልን! የልጆቻችንን ልብ ወደ ጫካ እያሸፈተች ነው።> ቢሉኝ እንደው ሳቄን መቆጣጠር ተሳነኝ ስልሽ! (አሁንም ከት ብሎ እየሳቀ) በሽመል ጦርነት ልትገጥሚ መሆኑ ነውኮ!!» እንባው እስኪወርድ ሳቀ። አጎቴ ሲያወራው ልጅነቴን ከመራራነቱ ይልቅ የተዋዛ ጨፍጋጋ ያደርገዋል። እያንዳንዷን ክስተት በቅደም ተከተል ሳይስት ሲያወራኝ ያኔ ተሰምቶኝ የነረውን ነገር ባላውቅም ዛሬ ላይ ግን ስሰማት ሜላት ምሬት ብቻ አልነበረችም።
17 ዓመት ሲሆነኝ ከአባቴ ሞት በኋላ ረጭ ብሎ የነበረው የሁለቱ ወገኖች ቁርሾ በሽመል የማይመከት የፀብ ጉርምርምታ ሆኖ ተጀመረ። ወጣቶቹ መሳሪያ ያለው በመሳሪያ የሌለው በጦር እና በጎራዴ እንዴት ጠላቶቻቸውን እንደሚመክቱ ሲመካከሩ አንደኛ የነገር ጠንሳሽ ሆኜ ተገኘው። ለካንስ ፀብ ፈጥሬ ቁምነገራቸውን ሳይቋጩ ስለምረብሻቸው ፈርተው ዝም አሉኝ እንጂ ከሴት ጋር በፀብ አውድማ መሰለፍን እንደውርደት ቆጥረውት ኖሮ ለአጎቴ መጥተው ነገሩት። ብመከር ብዘከር የ<አባቴን ገዳዮች፣ የእናቴን ደፋሪዎች የማገኝበት ብቸኛ አጋጣሚዬ ይሄ ነው። ቢከለክሉኝ ራሱ ተደብቄ እከተላቸዋለሁ።> ብዬ ፈረጠምኩ። የዛን ቀን በሩን ቆልፎብኝ የእህል ማዳበሪያ ሊቀበል ደርሶ እስኪመለስ የሳንቃውን በር ገንጥዬ ወንዶቹ የሚመካከሩበት ጫካ ሄጃለሁ። አጎቴ በጥቆማ ከቦታው ሲደርስ ከወንዶቹ መሃል ቆሜ <እኔ ነኝ ያለ ወንድ እጅ በእጅ አንድ ለአንድ ይግጠመኝ። አንዳችሁ ካሸነፋችሁኝ እቀራለሁ። አልበጠብጣችሁም። ሁላችሁንም ካሸነፍኩ ግን አብሬያችሁ እሄዳለሁ።> እያልኩ የሚጣላኝ ስጋብዝ ደረሰ። አጎቴ እንዳለኝ ከሴት ጋር ተደባድበው ቢሸነፉ ቅሌት እንደሆነ ስለገባቸው ሊደባደበኝ የደፈረ የለም። <መቼም አንቺም አንዱን ከጣልሽው በኋላ ወንድ ነኝ ያለ ደፍሮ ለመውደቅ አይመጣም ብለሽ እንጂ ያን ሁሉ ወጠምሻ እንደማትጥዪው ታውቂው ነበር።> አለኝ እንደመኩራት እያደረገው።
ከዛ በኋላ በምንም ሴትነቴ እንደማይመለስ ተስፋ ቆረጠ። እኔ እንዳላገኘው ደብቆ ያስቀመጠውን የአባቴን ሽጉጥ እና ታጣቂዎች በየቤቱ እየፈተሹ ነው ተብሎ ተቆፍሮ የተቀበረ ክላሽንኮቭ ጠመንጃውን አውጥቶ ሰጠኝ። ከመንደር አርቆ ወስዶ ኢላማ ያስለምደኝ ጀመር። አባቴ ከልጅነቴም መሰረታዊ ነገሮችን ከእናቴ ደብቆ ይዞኝ እየሄደ ያሳየኝ ስለነበር ብዙ አላስለፋሁትም። በመጨረሻም የአባቴን ገዳዮች የመጨረስ ሀሳብ ብቻውን ልቤን በሀሴት ሲሞላው ነው ሽማግሌ ልከው ፀቤ ላይ ውሃ የቸለሱበት።
ከእኔ ውጪ የቀረው ወጠምሻ መሳሪያውን ለታጣቂ አስረክቦ ጦርና ጎራዴውን ቀጥቅጦ የሽንኩርት መክተፊያ ቢላ አድርጎ ለሚስት እና ለእናቱ ሰጠ። ምንም እንዳልሆነ ሁሉ ሰላማዊ ህይወት መኖር ጀመረ። ጭራሽ ገበያ መሃል ሲገናኙ ሰላምታ መለዋወጥ ጀመሩ። ሚስቶች በመሃከላቸው ያለ የትዬለሌ ኪሎሜትር ርቀት ሳያግዳቸው ሽሮ መበዳደር ጀመሩ። እንደአጎቴ እምነት ከዚህ በኋላ ሴትነቴን ብቻ ሳይሆን ሰውነቴንም በከፊል ከዳሁ። የበቀል ጥሜን ያብርድልኝ እንጂ በመንገዴ የሚመጣ ማንም ሰው ቢሆን ከማስቀየም ወደኋላ የማልል አውሬ ሆንኩ። ቁጣዬን የምገልፅበት የማውቀው ብቸኛ መንገድ ፀብ ስለነበር <የምትጣዪው ብታጪ ከቆመ ግንድ ተጣልተሽ ትገቢ ነበር። የማደርገው ጭንቅ ጥብብ አለኝ።> ነበር ያለኝ አጎቴ። ሰላሙን የተቀበለ ሁሉ አጎቴንም ጨምሮ ጠላቴ ሆነ። መራር ሆንኩ። የቀን ተቀን የሆነ ቀን እንደምገድላቸው ነበር። አጎቴ በማያውቀው ምክንያት እንደዛ ሰፈርተኛውን እያሳቀቅኩ ግን ቆየሁ። አንድ ቀን ጭንቅህ ይብዛ ሲለው አንድ ወዳጁ ቲቪ ገዝቶ ሊያሳየን ተለማምኖ ይዞኝ እስከሄደ ቀን ድረስ። ቲቪ እንግዳ የሆነበት ብዙ መንደርተኛ ሰብሰብ ብሎ እስክሪኑ ላይ ባፈጠጠበት ያ ሰውዬ …… እናቴ ስትደፈር መጥቶ አይቶ ሱሪውን ሊፈታ ብሎ ሲጠራ የወጣው ሰውዬ አመዳም ካኪውን አውልቆ በውሃ ሰማያዊ ሱፍ ንግግር ያደርጋል። ሰውየው ሚንስትር ሆኖ ተሹሞ ብልግናውን ከአንድ ከተማ ወደ ሀገር አቀፍ የማዛመት እድል ከማግኘቱ በላይ የመንደሬው ማሽቋለጥ አንድዶኝ በጠበጥኩኝ።
«ሙሉሰውን አያችሁት? አሁንማ ጆሮው ቢቆረጥ የማይሰማ ባለስልጣን ሆነ።» እየተባባሉ ከዓመታት በፊት መንደራችንን አጋይቷት ፣ ሬሳ አስታቅፎን እየፎከረ እንደሄደ ረስተውት በኩራት ያወሩለታል። ብቻዬን የተበደልኩ አድርጌ የተሰበሰበውን ሰው ተሳድቤ ወጣሁ። በሚቀጥለው ቀን ኪዳንን አስከትዬ አጎቴ በሌለበት ቀዬውንም ለቅቄ ወጣሁ።
«ከዛስ?» አልኩኝ ተመስጬ ስሰማው ቆይቼ
«ከዛማ በእጄ ያሳደግኩሽ ልጄ ወሬሽን በእሩቅ የምሰማ ባዳዬ ሆንሽ። ብፈልግ ባስፈልግ እንዳትገኚ ስለፈለግሽ አጣሁሽ። አንቺም እንደእናትሽ ላትመለሺ መሄድሽን አምኜ ተስፋ በቆረጥኩ ሰዓት አንድ ቀን መንደርተኛው ጠላ ቤት ውስጥ ጉድ ጉድ እያለ ወሬ ሲፈጭ ደረስኩ። የምሽት የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ መታየትሽን <ልጅህ ዘንጣለች> ብለው ነገሩኝ። ምን ስታደርግ ታየች ብል <አታውቅም ኖሯል እንዴ የሚንስትሩ የሙሉሰው ሚስትም አይደለች? ከእርሱ ጎን ሆና ነው ባለፊልሙ የቀረፃት> ብለው መርዶዬን እንደምስራች ጋቱኝ።» ሲለኝ ጆሮዬም መሰለኝ።
«ሙሉ ሰው እናቴ……. » መጨረስ አንቆኝ ስንተባተብ
«ልትገያቸው ከመዘገብሻቸው ሰዎች መሃል ዋንኛውን ማግባትሽን ስሰማ የፍቅር እንዳልሆነ ጠርጥሬ ተከፋሁ። እንደባዳ ዜናሽን ከሰውም አይደል የምሰማው ? እንደፈራሁትም <ሚንስትሩ በገዛ ሚስታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ።> የሚለው ዜና ሀገሪቷን ይንጣት ጀመር።» ብሎ ኩርምት ብሎ ተከዘ።
እቤት ካዝና ውስጥ ያገኘሁት የጋብቻ ሰርተፊኬት ትዝ አለኝ። ሙሉሰው!! ጠላቴን ነው ያገባሁት? ምን ምክንያት ይኖረኝስ ይሆን?
.......... አልጨረስንም ...........
Join us
@hagerefic
26
3August 29, 2024 243