የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ አምስት) (ሜሪ ፈለቀ)… — Hagere~fic — TG.ME

#የመኖር አካፋይ ፣ የመ ፤ ሞ ፣ ት ሲሶ ፣ መንገድ መሃል ………… (ክፍል አስራ አምስት)
(ሜሪ ፈለቀ)

«አባቴም እንደእነሱ መጥፎ ሰው የነበረ ቢሆንስ? የሆነችን ልጅ አባት የገደለ ቢሆንስ? የሆነኛው ሰው ሚስት ስትደፈር ቆሞ አይቶ ቢሆንስ? መቼም ከተማቸውን በእሳት ሊለኩስ ሲሄድ <የእግዜር እንግዳ> ብለው አልተቀበሉትም! ተታኩሰዋል አይደል? በተኩሱ መሃል የገደላቸው ሰዎች እነሱም የሆነች ህፃን አባት ፣ የፀቡ ግብም አላማም ያልገባት የሆነች ምስኪን ሴት ባል ይሆናሉ።» አልኳት እናቴን ከቀናት ድንዝዝና እና ማሰላሰል በኋላ የሆነ ቀን። ከአሁን አሁን ትጎፈላለች ብሎ በዓነቁረኛ የሚከታተለኝ አጎቴ ዝግንን እያለው

«ውይ በስመአብ!!! እውነትም አባትሽን ዘንግተሽዋል። ምነው ልጄ? እሱ እንደው አንዳንዴ አጓጉል ጀብደኝነቱ ከልክ ያልፋል እንጂ እንዴት ያለ ለሰው አዛኝ እና ደግ ሰው መሰለሽ? አባትሽን መጥፎ ሰው? ኸረ ተይ መንደሬው እንዳይሰማሽ? የሀገሬው ሁሉ አጉራሽ አልባሽ ነበር።» አለኝ።

«ለወገኑ ነዋ! በመሰረቱ ሁለቱም ወገኖች ለየራሳቸው ወገን መከታ ለመሆን አይደል የሌላውን ወገን ሲያጠቁ የኖሩት። እነዛም ወገኖቻቸው የሚመሰክሩላቸው ደግ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናልኮ!! ምናልባትም <ማ? የእኔ አባት? እንኳን በሰው በዝንብ ላይ እጁን አያነሳም> የሚሉላቸው ልጆች ይኖሯቸው ይሆናል። ሁሉም ሰው በራሱ እስካልደረሰ በስተቀር ምክንያታዊ እና ልክ ነው። በራሱ ሲደርስ ነው ሚዛናዊነቱን የሚያጣው። ለምሳሌ የእኛዎቹ ተደፈርን ብለው ሲያስቡ ከተማቸው ድረስ ሄደው አጥቅተው ሲመለሱ፣ የሰራነው ልክ አይደለም ብለው ለአንዴ እንኳን ተፀጽተዋል? ምናልባትም ልክ አይደላችሁም ያለ አዋቂ ይኖር ይሆን? እስቲ ለትውልድ የሚሻገር ቁርሾ ከማኖራችን በፊት ሳንጫረስ መፍትሄ እንፈልግ ያለ ይኖር ይሆን? እነዛ ተመሳሳዩን ሲያደርጉ ህመማችንን የምናየው ከእኛ ወገን ስለሆነ አውሬነታቸው እና እንስሳነታቸው ነው የታየን። » አልኩኝ። እናቴ ፈገግ አለች።

«ምነው?» አልኳት

«ኸረ ምንም አለች!» አሁንም ድካም በተጫነው ፊቷ ላይ ፈገግታ እየነገሰ።

«እንዴ አስካል እንዲህማ ፊት አትስጫት!! የአባቷንም ነፍስ መና ማድረግ ነው። ሰው ነውና ምኑንም ያህል ጥፋት ባይጠፋው፣ ህይወቱን ጭምር የገበረው ለዝህች መንደር ነው። ያ መረሳት የለበትም!!» አለ የእውነቱን እየተቆጣ!! ምናልባት ሰው የመሆን የአፈር ልውሳችን ውስጥ ያለ ነገር ይሆን? የእኛ ወገን ቢያጠፋም ( ወይም እናውቃለን አጥፍቷል) ቢሆንም የእኛ ወገን ስለሆነ ጥፋቱ እናኮስስለታለን። ከዛሳ? ከዛማ የእሱን ሀጢያት ደርምሰን የኛ ወገን ላልሆነ እንደርባለን። ከዛማ በንፅፅሮሽ የኛ ወገን ለመልዓክ የቀረበ ፃድቅ አድርገን እናርፈዋለን!! አጎቴ ሰሞኑን ከሚነግረኝ የመንደራችን ታሪክ በብዙ የተረዳሁት ያንን ነው።

«አዛኝቷን ነው የምልሽ እንዲህ ተልፈስፍሰሽስ ከማይ ከነማስጨነቅሽ የድሮዋ ሜላት ትምጣብኝ!!» ሲለኝ እናቴ በተሟጠጠ አቅሟ ልትነሳ ሁላ ቃጣት። «እረፍ ብያለሁ!» ብላ ጮኸች ፣ አጎቴ አፍንጫውን እየነፋ ወጣ!

ማለቂያ የሌለው የጥያቄ ጎርፍ ሳንፎለፉልለት ቆይቼ አጎቴ ከነገረኝ ገጣጥሜ የገባኝ እድገቴ እንዲህ ነው። ከዛን የመዓት ቀን በኋላ እናቴ የሆነችውን ለወንድሟ ነግራው አባቴ እንኳን ሳይቀበር እኛን ትታ ተሰደደች። አጎቴ ልጅም ሚስትም ያልነበረው ላጤ ስለነበር ምድር ዞሮበት እንደነበር ነገረኝ። አባቴንና በዛን ቀን በሞት ያጣናቸውን ወገኖቻችንን ቀብረን መንደሬው ማቁን እንደለበሰ ከረመ። ከዛን ቀን በኋላ ቀሚስ ጠላሁ። ስለብሳቸው ቀሚስ የሚያካክሉትን የአባቴን አላባሾች መልበስ ጀመርኩ። ቁጭ ብዬ የአባቴን ሱሪዎች ለእኔ እንዲሆኑ ቆርጬ እና ሰፍቼ መልበስ ጀመርኩ። አንድ እለት ለበዓል በጌጥ ያሸበረቀ ቀሚስ ገዝቶልኝ መጣ።

«እኔ ይሄን አልለብስም! ሴት መሆን አልፈልግም።» አልኩ። ምናልባት በሴትነት ውስጥ የእናቴን ስቃይ በወንድነት ውስጥ የአባቴን ጀግንነት ነድፌ ይሆናል እናቴን ከመሆን አባቴን ሆኜ ሞትን እንኳን ለመግጠም ራሴን መሞረድ የጀመርኩት። ሴት ሊያደርጉኝ የሚችሉ ድርጊቶችን ማጀትን ጀምሮ ሸሸሁ። አጎቴ ትምህርት ቤት ከኪዳን ጋር ቢልከንም ትምህርቴን አልቀጥልም ብዬ አሻፈረኝ አልኩ። ትኩረቴ ሁሉን ሁሉ ጉልበት እና ጡንቻ ማካበት ላይ አደረግኩ። ውሎዬ ከጎረምሳ ጋር ኳስ መራገጥ ፣ ጅራፍ ማጮህ ፣ እንደእኩዮቼ ወንዶች ጡንቻ መለካካት ፣ ከሰፈሩ ፈልፈላ ጋር ሜዳ ላይ ማን ስንት ፑሽ አፕ ይሰራል አፈሩን ስንልስ መዋል ፣ የሰፈሩን አህያና ውርንጭላ ሁላ መጋለብ ….. ሆነ። ይሄን ሲነግረኝ አጎቴ ፈገግ ብሎ

«በአዛኝቷ! እንደው ሞገደኛ ነበርሽኮ!! ቆሜ ካልሸናሁ ብለሽ ጉድ አፍልተሽ ነበርኮ!» ብሎ ክትክት ብሎ ሳቀ። ቆሞ እንደወንድ የመሽናት ሀሳቡ አብሬው እንድስቅ አደረገኝ።

በየቀኑ የምደባደበው ሰው ፈልጌ ተደባድቤ እገባለሁ። በምለብሰው የአባቴ ልብስ ሲስቁብኝ እጣላለሁ። ሁሌም አሽተው አሰባብጠው ይለቁኛል በነገታው አሁንም ነገር ፈልጌ እወቀጣለሁ። በተለይ ትልቁ ገበያ ስንሄድ ከጠላቶቻችን ወገን የሆነ ሰው ከገጠመኝ ፍፃሜዬ ደማምቶ መምጣት ቢሆንም ነገር ከመፈለግ አልቦዝንም። በዱላ ብዛት የትኛውም ድብደባ ቅም የማይለኝ ደነዝ ሆንኩ። ቁጥር አልባ ቡጢ እና ሽመል ከፈጀሁ በኋላ አንድ ቀን አሸንፌ መጣሁ። ውጤቱ ማሸነፍ ሆነ እንጂ አፍንጫ እና ጉንጬ እስኪደባለቅ ተወግሬ ነበር።

«በጭራሽ አልገባኝም ነበር። <እንደው ከዚህ ሁሉ ምናለ ድብድቡ ቢቀር? መቼም አንድ ቀን አንዱ አጉል ቡጢ የሰነዘረብሽ እንደው 32 ጥርስሽን በእጅሽ ይዘሻት መምጣትሽ ነው። እንደው ምን ባደርግሽ ይሻለኛል?> ስልሽ <ተደባድቤ ጉልበቴን ካልፈተንኩ እንደምችላቸው በምን አውቃለሁ? ድንገት ብንገጣጠም ሽመል ወይ ኮረት ፍለጋ ልዟዟር ነው?> ብለሽ መለሽልኝ። ለካንስ አጅሪት አባትሽ ከሞተ ቀን ጀምሮ የአባትሽን ገዳዮች እንዴት እንደምትበቀዪ ስታሰዪ ነው ውሎ አዳርሽ።» አለ በሰዓቱ ስላልተረዳኝ እየከፋው።

ወንድ የመሆን ትጋቴን መቼም እንደማላቆም ሲያውቅ ፣ በራሴ ልጅነት ውስጥ መኖሬን አቁሜ በአባት እና በእናቴ በደል ውስጥ እየዋኘሁ እንደሆነ ሲረዳ ለምኜው እንቢ ብሎኝ የነበረውን የሆነ ከከተማ የመጣ ልጅ የእድር ቤቱ አዳርሽ ውስጥ የሚያስተምርበት ካራቴ ቤት በ15 ዓመቴ አስመዘገበኝ። እንደዛ ቀን የተደሰትኩበትን ቀን አይቶ እንደማያውቅ ነገረኝ። ኪዳንን ትምህርት ቤት አድርሼ የምመልሰው እኔ ነበርኩ። በኮባ የተሰራ ጠብመንጃ ትከሻዬ ላይ አንግቼ ፣ እንጨት ፈቅፍቄ የሰራሁትን የእንጨት ሽጉጥ ወገቤ ላይ ሽጬ …….. ከፍተኛ ጥበቃ እያደረግኩለት እንደሆነ አስመስላለሁ። ሰውነቴ እየፈረጠመ ….. ልቤም በማንአለብኝነት እያበጠ ….. <ፀብ ሆይ ወዴት ነህ?> ብዬ እያልኩ ማሸበር ስጀምር ….. የሰፈሩ ሰው ወንድ ልጆቻቸውን እንኳን <እሷ የሴት ተፈጥሮ አልፈጠረባትም። ወንዳወንድ ናት ከእርሷ ጋር እንዳትገጥሙ> እያሉ መከልከል ሲጀምሩ ……. የጠገበ ልቤን የሚወጥር ሙገሳ ጆሮዬ ገባ። ኪዳን ከልጆች ጋር ተጣልቶ ሲያለቅስ የሰፈር ማቴ ለእኔ ሊያሳብቅ ሲሮጥ አንድ አልፎ ሂያጅ
👍22🥰1
August 29, 2024 258