ፍልስፍና እና የፍልስፍና አባባሎች: post #444 — TG.ME

#የምስራቃውያን_ተረት

አንድ ኃያል ንጉስ ከአስፈሪ የሞት ፅልመት ጋር ተገናኘ። ለቀናትም ከፊቱ የተደቀነው የሞት ጥላ እንቅልፍ ነሳው። "ማነህ አንተ? ምንስ ትፈልጋለህ?" ሲል ጠየቀው በድንጋጤ። ጥቁሩ የጥላ ምስልም "እኔም ሞትህ ነኝ። የመጣሁትም በትክክለኛው ስዓት እና ስፍራ እንዳገኝህ ላስታውስህ ነው።" አለው። ከንጉሡ ፊት ከመሰወሩ በፊትም "ነገ በትክክለኛው ስፍራና ስዓት እንገናኝ " ብሎት ሄደ።


በማስጠንቀቂያው የተደናገጠው ንጉሥ፤ ጠቢባን አማካሪዎቹን፣ ኮከብ ቆጣሪዎችን፣ ህልም ፈቺና ጠንቋዮችን አስጠርቶ የህልሙን ምንነት እንዲያስረዱት ጠየቀ።

ጠቢባኑ በንጉሡ እልፍኝ ተሰብስበው መከራከር ጀመሩ። ንጉሱን ከህፃንነቱ ጀምሮ የሚያውቁት አንድ አዋቂ ወደ ጆሮው ተጠግተው እንዲህ ሲሉ መከሩት፦ "የጊዜህን አታባክን የነዚህ ጠቢባን ክርክር አያልቅም። ቀኑ ያልቅና በነጋው ዕለት ይተካል። ስለዚህ ፈጣኑን ፈረስ ጫንና ከዚህ ስፍራ አምልጥ!"

ንጉሱም ፈጣኑን ፈረስ እየጋለበ ህልሙን ካየበት ቤተ መንግሥቱ ራቀ። ከከተማዋ ብዙ ርቀት ጋልቦ ቆመና "ሞት እዚህ ድረስ ሊመጣብኝ አይችልም በትክክለኛው ሥፍራና ሰዓት አልገኝለትም" አለ።

ፀሀይ ለማጥለቅ ስትቃረብ ፈረሱን አሳርፎ ምግብ ሰጠው። በፈረሱ ፈጣንነትና ከሞት መራቁ ተደስቶ ሳር ላይ ሲቀመጥ ትከሻውን አንድ ነገር ዳበሰው። ዞሮ ሲመለከት የሞት ጥላው ከኋላ ቆሞ በፈገግታ ያየው ነበር። "ምን ያስቅሃል?" ሲል የተደናገጠው ንጉሥ ጠየቀው።
ሞትም "የቀጠሮአችን ጊዜና ቦታ ይህ ነው። በቶሎ አትደርስም ብዬ ሰግቼ ነበር። ሆኖም ግን ለፈረስህ ምስጋና ይግባውና አልዘገየህም" ሲል መለሰለት።
October 7, 2021 20.7K 82