ፍልስፍና እና የፍልስፍና አባባሎች: post #441 — TG.ME

ለሆዳቸው ሲሉ ሕሊናቸውን የጣሉ ትርፋቸው ምንድነው??
(እ.ብ.ይ.)

ወዳጆች ቅንነትን የሚያወድም፣ ደግነትን የሚያጠፋ፣ ፍቅርን አሽቀንጥሮ የሚጥል ልቡ በክፉ ሃሳብ የጠፋ ብቻ ነው፡፡ ብዙዎች በውስጣቸው ያለውን ቅንነት፣ በልባቸው የነበረውን ደግነት፣ በሕሊናቸው የኖረውን መልካምነት አሟጥጠው በመጨረስ ከሠውነት ጎዳና ይወጣሉ፡፡ ከትክክለኛው የሠውነት ምልክታቸው ያፈነግጣሉ፡፡ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከደግነት ይልቅ ክፋት ዓይናቸውን ያውረዋል፡፡ ልባቸው በክፉ ሃሳብ ይጨልማል፡፡ በጨለማው ማንነታቸው ዓለሙን ይበይናሉ፡፡ በበየኑት ዓለም ውስጥ በድቅድቁ አመለካከታቸው ብቻ ነው የሚመላለሱት፡፡ ልቦናን መጣል፣ እውነትን ማርከስ፣ እምነትን ማጉደል ለነሱ ቀላል ይሆናል፡፡

ሠው ለእምነቱ፣ ለእውነቱ፣ ለሕሊናው መኖር ካልቻለ ታዲያ ለምን ሊኖር ነው?? ሠው በሆዱ፣ በቁስ ፍላጎቱ፣ በብልጭልጩ ዓለም እየታለለ እስከመቼ ይዘልቃል?? የሠውነት ውስጣዊ ዓለሙንስ የሚያረካው መቼ ነው?? የቱ ላይ ነው ሠውነቱ?? ለሆዳቸው ሲሉ አዕምሯቸውን የጣሉስ ትርፋቸው ምንድነው??

ታላቁ ቡድሃ ‹‹ምንም ዓይነት መርዝ ቀና አሳቢን አይገድለውም፡፡ ምንም ዓይነት ሕክምና ክፉ አሳቢን አያድነውም፡፡›› ይለናል፡፡

እውነት ነው! ክፉ ሃሳብን፣ ተንኮልን፣ ሌሎችን ማሳቀቅን፣ እኔ ብቻ ይድላኝ የሚል ስግብግበነትን፣ ሌሎች በየሜዳው ቢወድቁ እኔ ምን ተዳዬ የሚል ጨካኝ አመለካከትን ማከም መቻል እጅግ ከባድ ነው፡፡ በሽተኛው በሽታውንና ህመሙን ተረድቶ ለመፈወስ እስካልቆረጠ ድረስ ሊታከም የሚችል በሽታ አይሆንም፡፡

በዛው ልክ ደግሞ ቀና አስተሳሰብን የሚያወድም ምንም ዓይነት ሃይል የለም፡፡ ቀና አሳቢው ቢሞት እንኳን ቅንነቱን ሌሎች ላይ አጋብቶ ስለሚኖር በቅኖች ቅብብል ቀና አስተሳሰብ ዘላለም ይኖራል፡፡ ቀና አስተሳሰብ ባይኖር ክፉ ሃሳቦችን ለመመዘን አንችልም ነበርና፡፡

ኤሪክ ፎረም የተባለ ፀሐፊ You shall be as Gods በተባለ መፅሐፉ እንዲህ ይለናል፡-

‹‹ክፋት የሚመገብ አዕምሮ በክፋት ያድጋል፡፡ ደግነትም የሚመገብ እንዲሁ ይሆናል፡፡ የዕድገት ዋነኛ ምክንያት ግን የሠው ብቸኛ ችሎታ በሆነው ማሠብ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡›› ይለናል፡፡

እውነት ነው! ሠው ሆዱን ለሚመግበው እንደሚጠነቀቀው ሁሉ ለአዕምሮውም የሚመግበውን ሃሳቡን መፈተሸ አለበት፡፡ ያገኘውን ሁሉ አግበስብሶ የሚመገብ ከሆነ ጉዳቱ ለራሱ ነው፡፡ ቁንጣንም በሽታ ነው፤ በበቂ ሁኔታም አለመመገብ የምግብ እጥረት ነው፡፡ መጠን ግድ ይላል፡፡ መጠን እንወቅ ወዳጆች!

ለዚህም ነው ኤሪክ ፎረም፡- ‹‹የሠው ልጅ እጅግ ጨካኝም ሆነ እጅግ ደግ የሚያደርገው ዘወትር ሃሣቡን የሚመግበው ነገር እንጂ ሌላ የተለየ ምክንያት ኖሮት አይደለም፡፡›› በማለት ሠው ሃሳቡ ላይ ብዙ መስራት እንዳለበትና ሚዛን የሚደፋ ሃሳብ ተመግቦ እንዲያመርት ነው ፀሐፊው የሚመክረው፡፡

አንዳንድ ሠው ደግሞ ራሱን ለክፋት አስተሳሰብ እያጋለጠና በፍቃዱ ጨካኝ ሃሳብ በአዕምሮው እየሞላ ይሄን ያደረግኩት ሠይጣን አታሎኝ ነው እያለ ራሱን ያሞኛል፡፡ ራሱ ለፈጠረው ስህተት ከመናዘዝ ይልቅ ሠበብን ፍለጋ ይዳክራል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሠው ለሠራው በጎ ነገር ዕውቅናን ለማግኘት ደፋ ቀና ቢልም፤ ለሠራቸው ስህተቶች ደግሞ ሃላፊነትን መውሰድ አይሻም፡፡ ሌሎች ላይ ማላከክ፣ ሠበብ መፈለግ፣ የእምዬን ወደአብዬ ማድረግ ከስህተቱ ለመታረም ያለመቻላችን ውጤት ነው፡፡

አንድ የሱፊ ተረክ አለ፡፡ በኢራን አቡል ቢስታሚ የተባሉ በእምነታቸው ፅኑ እና የታወቁ ሱፊ ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ምሽት ከደቀመዛሙርቶቻቸው ጋር ተቀምጠው ሲያወጉ የእምነት ጉዳይ ተነሣ፡፡ ደቀመዛሙርቱ ተራ በተራ የእምነታቸውን መላላትና ብሎም መጥፋት ከነገሯቸው በኋላ ለዚህም ምክንያቱ ሠይጣን እንደሆነ አስረግጠው አስረዷቸው፡፡

በዘመኑ ተዓምራትን ማድረግ ይችሉ ነበር የሚባልላቸው አቡል ቢስታሚ የደቀመዛሙርቱን ስሞታ ካዳመጡ በኋላ ሠይጣንን ጠርተው ጠየቁት፡-

‹‹እውን የደቀመዛሙርቶቼን እምነት ሠርቀሃል?›› አሉት፡፡ ሠይጣንም መለሠ፡- ‹‹እኔ የማንንም እምነት ለመስረቅ የሚያስችል ሃይል የለኝም፡፡ ምክንያቱም የሚያምኑት አምላክ ከእኔ የላቀና እጅግም ከፍ ያለ ሃይል ያለው ነውና፡፡ ነገር ግን ብዙዎች በየጥቃቅኑ ምክንያት እምነታቸውን በየመንገዱ እየጣሉ ሲሄዱ አግኝቼ በመሠብሠብ ከእኔ ዘንድ ያስቀመጥኩትን እንደሠረቅሁ አድርገው እየዋሹ ነው፡፡›› በማለት መለሠ፡፡

አቡል ቢስታሚም ደቀመዛሙርቱን ከሠይጣን ጋር ላኳቸውና እንዲህ አሉ፡-

‹‹እምነቱን የጣለ ታግሎ ያስመልስ፡፡ ሠይጣን ያለጥፋቱ ምን ባደረገ ይቀጣ?›› በማለት ወሠኑ፡፡ እስከዛሬ ደቀመዛሙርቱ ወደቢስታሚ አልተመለሱም ይባላል፡፡

ወዳጆች ምንድነው በዓለም ያለን ትርፍ?? ካነሳነው ይልቅ የጣልነው አይበልጥም?? ምንድነው የዕድሜአችን ዓላማ?? በዕድሜአችን ውስጣችንን ካስደሰትንበት ይልቅ የተከፋንበት አይበልጥም?? የምንኖረው ለመብላት ብቻ ነውን?? የሐገርን ሃብት ለብቻ በጉልበትና በተንኮል እየመዘበሩ መኖር ጥቅሙስ፣ ሠበቡስ፣ ትርፉስ፣ ውጤቱስ ምንድነው?? የተለየ ግቡ ምንድነው?? ሕሊናን፣ ልቦናን፣ ነፍስያን፣ መንፈስን የሚያረካውና የሚያጠግበውን ፍላጎታችንን እንዴትስ ነው ልናረካው የምንችለው??

ለማንኛውም ለሆዳችን ብቻ ሳይሆን ለውስጣችንም፣ ለነፍሳችንም፣ ለህሊናችንም፣ ለልባችንም እኩል በእኩል እንኑር የዛሬው መልዕክት ነው!

ቸር ጊዜ!

__________________
(እ.ብ.ይ.)
October 6, 2021 22.3K 36