ERA ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር: post #4839 — TG.ME

የአርባምንጭ - ኮንሶ - ጂንካ መንገድ ጥገና በትኩረት እየተከናወነ ነው
 
አርባምንጭ፣ ነሐሴ 07/2018 ዓ.ም (ኢ መ አ)፦ የአርባምንጭ - ኮንሶ - ጂንካ መንገድ ጥገና በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል። ጥገናው የመንገዱን የአገልግሎት ደረጃ ከማሻሻሉም በላይ የተጠቃሚዎችን የጉዞ ጊዜ፣ ወጪ እና እንግልት በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው።
 
የ235 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መንገድ፣ 211 ኪሎ ሜትር የድርብ አስፋልት ወለል ንጣፍ እና 24 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ያካተተ ነው። መንገዱ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ለትራፊክ ክፍት ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
 
የመንገዱ የአገልግሎት ዘመን መጠናቀቅ፣ የትራፊክ ፍሰት መጨመር እና ተሽከርካሪዎች ከሕግ በላይ ጭነት መጫናቸው ለመንገዱ መበላሸት ዋና ምክንያቶች ናቸው። ይህም በትራንስፖርት እንቅስቃሴው እና በማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮ ቆይቷል።
 
ይህን ችግር ለመቅረፍ የሶዶ መንገድ አውታር አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት (ዲስትሪክት) በጣም የተጎዱ ክፍሎችን በመለየት፣ በተለያየ ደረጃ የጥገና ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
 
የጥገና ሥራው የአስፋልት መደረብ፣ የተቦረቦሩ ክፍሎችን በአስፋልት መሙላት፣ የመንገድ ትከሻ ማደስ፣ የጎርፍ ውሃ ማሳለጫ ቦዮችን ማጽዳት እና የተበላሹ ክፍሎችን መልሶ ማጠናከርን ያካተተ ነው። በተጨማሪም የዚሁ መንገድ አካል የሆነው የወዘቃ - ጋቶ የጠጠር መንገድ ሙሉ በሙሉ ተጠግኗል።
 
በአሁኑ ወቅት ከታቀደው 179 ኪሎ ሜትር የጥገና ሥራ ውስጥ 147 ኪሎ ሜትሩ በመጠናቀቁ የ82 በመቶ አፈጻጸም ተመዝግቧል። ከዚህ ውስጥ 129 ኪሎ ሜትሩ የአስፋልት፣ 18 ኪሎ ሜትሩ ደግሞ የጠጠር መንገድ ጥገና ነው።
 
መንገዱ በመጠገኑ በተጠቃሚዎች ላይ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል። ከዚህ በፊት 6 ሰዓት ይፈጅ የነበረው ጉዞ በአሁኑ ወቅት ወደ 2 ሰዓት ዝቅ እንዲል አስችሏል። በተጨማሪም የትራንስፖርት ወጪ እና የአደጋ ሥጋት እንዲቀንስ አግዟል። ከዚህም ባለፈ የአሽከርካሪዎችን እንግልት፣ የተሽከርካሪ የጥገና እና የመለዋወጫ ወጪን ለመቀነስ ረድቷል።
 
ቅርንጫፍ ጽ/ት ቤቱ ቀሪዎቹን ውስን የጥገና ሥራዎች በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል።

ኢትዮጵያን የማገናኘት 75 ዓመታት
መንገዳችን፤ ኃላፊነታችን!

በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል [email protected]
› ዩቲዮብ www.youtube.com/@ethioroads
❤7👍1
August 13, 2026 5.3K 2