የጎንጂ-ቆለላ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት 98.82 በመቶ አፈጻጸም ላይ ደረሰ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢመአ)፤ በጎንጂ ቆለላ ወረዳ የሚገነባው የቆሬ - አዲስ ዓለም የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት የ10.59 ኪሎ ሜትር ግንባታን በማጠናቀቅ 98.82 በመቶ አጠቃላይ አፈጻጸም ላይ ደርሷል። ከባህር ዳር ወደ ሞጣ በሚወስደው መንገድ ላይ ከምትገኘው ቆሬ ቀበሌ ተነስቶ ምስራቅ አቅጣጫ በመጓዝ ሂዳሴ መንደርን አቋርጦ አዲስ ዓለም ከተማ የሚገባው ይህ ፕሮጀክት፣ በአጠቃላይ 10.74 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ቀድሞ የነበረውን የጠጠር መንገድ ወደ አስፋልት ደረጃ የሚያሳድገው ይህ ግንባታ፣ የመንገዱ ስፋት በገጠር 10 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትር እንዲሁም በወረዳ 21.5 ሜትር ሆኖ እየተገነባ ይገኛል።
ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን በአካባቢው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አዲስ ተስፋ ይዞ ይመጣል። በተለይም አርሶ አደሩ በአካባቢው በስፋት የሚያመርታቸውን እንደ ጤፍ፣ ሰሊጥ፣ በርበሬና ማሽላ ያሉ የግብርና ምርቶችን ያለምንም እንግልት በወቅቱ ወደ ገበያ ለማቅረብና የቱሪዝም መዳረሻዎችን በቀላሉ ለማገናኘት ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ከዚህም በላይ ነዋሪዎች ቀድሞ ለመጓጓዝ ይወስድባቸው የነበረውን የጉዞ ጊዜ በአንድ ሰዓት ያህል በማሳጠር የዕለት ተዕለት ህይወታቸውን ያቀልላቸዋል።
ይህ ታላቅ ተስፋ የተሰነቀበት ፕሮጀክት ግንባታው እስከአሁን ድረስ ያጋጠሙና በሥራው ፍጥነት ላይ ጫና ያሳደሩ እንደ የጸጥታ፣ እና የወሰን ማስከበር ችግሮች እንዲሁም የነዳጅ እጥረት ተግዳሮቶችን ቀርፎ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል። ሥራው እንዳይቋረጥ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት፣ ለግንባታው የሚሆን ነዳጅ በቅድሚያ እንዲያገኝ በማድረግና ከፍተኛ ክትትል በማድረግ የተከለሰው የፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ ቀን በጥቅምት ወር 2019 ዓ.ም እንዲሆን ተደርጓል።
የበጀት ፍሰቱን በተመለከተ ቫትን ጨምሮ ከ333 ሚሊዮን ብር በላይ የተመደበለት ሲሆን፣ የስራ ተቋራጭነቱን ኅብር ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲያከናውነው የሃይዌይ ኢንጂነርስ ኤንድ ኮንሰልታንትስ ኃ/ተ/ግ/ማ ደግሞ የአማካሪነት ሚናውን እየተወጣ ይገኛል። ተቋራጩ አፈጻጸሙን እንዲያሻሽልና ቀሪ ሥራዎችን በተያዘው የበጀት ዓመት እንዲያጠናቅቅም በየደረጃው ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገለት ነው።
በአሁኑ ወቅት የጠረጋ፣ የአፈር ቆረጣና ሙላት፣ የሰብ ቤዝ፣ የቤዝ ኮርስ ንጣፍ እንዲሁም ሙሉ የ10.74 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ንጣፍ ሥራዎች 100 በመቶ ሙሉ በሙሉ ተጠናቀዋል። በተጨማሪም የፍሳሽ ማስወገጃ (ድሬኔጅ) ሥራው 98.58 በመቶ ላይ የደረሰ ሲሆን፤ እንደ እግረኛ መንገድና የመንገድ ምልክቶች ያሉ ቀሪ ሥራዎችንም 50 በመቶ በማድረስ ፕሮጀክቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ማጠናቀቂያው ምዕራፍ ለማሸጋገር የመጨረሻ ደረጃ ሥራዎች በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል [email protected]
› ዩቲዮብ www.youtube.com/@ethioroads
August 31, 2026 450 1