የሶዶ መንገድ አውታር አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት 1,890 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና አከናወነ፤ አፈጻጸሙም 96.3% ሆኖ ተመዝግቧል
ሶዶ፣ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም(ኢመአ): በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ስር የሚገኘው የሶዶ መንገድ አውታር አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በ2018 በጀት ዓመት ያቀዳቸውን የፊዚካልና የፋይናንሻል የሥራ ግቦች በስኬት አጠናቀቀ። ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 1.81 ቢሊዮን ብር በጀት መድቦ የነበረ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1.56 ቢሊዮን ብሩን (86.18%) ለተለያዩ የጥገናና መሰረተ ልማት ሥራዎች ማዋል ችሏል።
በፊዚካል አፈጻጸም ረገድም ከተቀመጠው 1,963 ኪሎ ሜትር የጥገና ዕቅድ ውስጥ 1,890 ኪሎ ሜትር በማጠናቀቅ 96.3% አፈጻጸም አስመዝግቧል።
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 3,242.5 ኪሎ ሜትር የመንገድ ሽፋን ያስተዳድረል፡፡ ከዚህም ውስጥ 68 በመቶው (2,196.5 ኪ.ሜ) የአስፋልት ኮንክሪት ሽፋን ሲሆን ቀሪው 32 በመቶው (1,046 ኪ.ሜ) በጠጠር የተሸፈነ መንገድ ነው። በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ዋና ዋና የጥገና ሥራዎች ዝርዝር አፈጻጸም እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
መደበኛ ጥገና፡ በበጀት ዓመቱ በከፍተኛ ትኩረት የተከናወነ ሲሆን በፋይናንሻል በኩል ከተመደበው 920.46 ሚሊዮን ብር በላይ 983.30 ሚሊዮን ብር (106.83%) ወጪ ተደርጎበታል። በፊዚካል በኩልም 1,731.02 ኪ.ሜ መንገድ በመጠገን የ98.33% አፈጻጸም ታይቷል።
ወቅታዊ ጥገና፡ በቅርንጫፉ የራስ ኃይልና በግል ተቋራጮች በጋራ የተከናወነ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 445.41 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ 157.57 ኪሎ ሜትር መንገድ ወቅታዊ ጥገና ተደርጎለታል።
ከባድ ጥገና፡ 1.20 ኪሎ ሜትር መንገድ የተጠገነ ሲሆን 67.03 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል።
የድልድይ መልሶ ግንባታ፡ ከተመደበው 3.23 ሚሊዮን ብር በጀት 100% ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ በመዋል ተጠናቋል።
የደህንነትና የመሬት ናዳ መከላከል፡ ለድንገተኛ አደጋዎችና ለመሬት ናዳ መከላከያ ሥራዎች ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ከአደጋ ስጋት ነጻ እንዲሆን አስችሏል።
ጽሕፈት ቤቱ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ የግብዓት እጥረቶች ቢያጋጥሙትም፣ የኪራይ መሣሪያዎችን በመጠቀምና የውስጥ አቅምን (የራስ ኃይልን) በማጠናከር ችግሮቹን መፍታት ተችሏል። ለ2019 በጀት ዓመትም በበጀት ዓመቱ የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን (የቡድን ሥራ፣ የሠራተኞች መዝናኛና የሕፃናት ማቆያ ግንባታዎችን ማጠናቀቅን ጨምሮ) እንደ ግብዓት በመውሰድ ለዋና ዋና መንገዶች (Trunk Roads) ልዩ ትኩረት በመስጠት ለመስራት ታቅዷል።
በተጨማሪ
› አጭር መልዕክት 8561
› ፖስታ ሳጥን ቁጥር 1770
› ድህረገጽ www.era.gov.et
› ፊስቡክ https://www.facebook.com/www.era.gov.et
› ቴሌግራም https://t.me/ethioroads
› ትዊተር https://twitter.com/EthiopiaRoadsAd
› ኢንስታግራም https://www.instagram.com/ethioroads
› ኢሜል [email protected]
› ዩቲዮብ www.youtube.com/@ethioroads
















