ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ስነ-ምግባር ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ተባለ፡፡…

ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ስነ-ምግባር ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ተባለ፡፡

በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ዓለም አቀፉ የፀረ ሙስና ቀን በዓለም ደረጃ ለ23ኛ ጊዜ በአገራችን ለ22ኛ ጊዜ “ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን ሰንሰለት እንበጥስ” በሚል መሪ ቃል ከከተማ አመራሮች እና ሰራተኞች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በማካሄድ ተከብሯል፡፡

በመድረኩ ላይ የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ስነ-ምግባር መኮንን አቶ ይመኑ አለኸኝ ከሙስና ምንነት አስከፊነትና መከላከል፣ ከስነ- ምግባር ግንባታ፣ ከተቋማት አሰራር ማዘመን እና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰነድ እንዲሁም እንደ ከተማ አስተዳደር እየተሰሩ ያሉትን ስራዎች አስመልክተው መነሻ ሀሳቦችን አቅርበዋል፡፡

ሙስና መፍረስ፣ መበስበስ፣ ያልተገባ ድርጊት መፈፀም እንደሆነ እና የሙስና ወንጀል የአሰራር ስርዓቶችን በማዛባት የህዝብና የመንግስትን ሃብትና ንብረት ለግል ጥቅም የማዋል አስከፊ ወንጀል መሆኑን አንስተው ወንጀሉ በህዝብና በመንግስት እንዲሁም በአገር ላይ ትልቅ ተግዳሮት በመፍጠር ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ሙስና ውስብስብና አደገኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ የዓለም መንግስታት ችግሩን በጋራ ለመታገል ስምምነት አጽድቀው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን አገራችን ኢትዮጵያም ሙስናን ለመታገል ህጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን በማውጣትና በስራ ላይ በማዋል በርካታ ጠቃሚ ስራዎች የሰራች ቢሆንም የሙስና ወንጀልን አስከፊነት ተረድተን የተቀናጀ የፀረ-ሙስና ትግል ባለማድረጋችን መሰረታዊ ለውጥ አላመጣንም ብለዋል፡፡

አቶ ይመኑ አክለውም ለሙስና እና ብልሹ አሰራር መፈጠር በምክንያትነት የሚጠቀሱ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ዋናው ችግር ግን የስነ-ምግባር ዝቅጠት እንደሆነ ጠቁመው ከችግሩ ለመውጣት ስነ-ምግባር ግንባታ ላይ በትኩረት ይዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡ እንደ ከተማ አስተዳደር ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን እና መሻሻሎች መኖራቸውንም ተናግረው ተቋማትን በማዘመን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ አሰፋ ይስማው በበኩላቸው እንደገለጹት ሙስና እና ብልሹ አሰራር ከራስ ወዳድነት፣ ሳይሰሩ ከመበልፀግ እሳቤ፣ ከማህበበረሰቡ እሴትና ልማድ ጋር በሚጣረስ ሁኔታ የሚፈፀም መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ለማስቀረት በስነ-ምግባር የተገነባ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የሙስና ወንጀልን ለመከላከል ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር፣ ግልጽፀኝነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን ማስከበር፣ ሀብትን ማስመዝገብ፣ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት እና ሌሎችንም ስራዎች መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተው ሙስና እና ብልሹ አሰራርን በተቀናጀና በተደራጀ መንገድ መታገል ይገባል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ አካላትም በሰጡት ሀሳብ በአሁኑ ጊዜ ሙስና እና ብልሹ አሰራር በስፋት መኖሩን አንስተው ከችግሩ ለመውጣት በጋራ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው ድርጊቱን በሚፈጽሙ ወንጀለኞች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ትውልድን በስነ-ምግባር መገንባት እና ተቋማትን በአሰራር ማዘመን እንደሚያስፈልግ ጠቁመው አመራሩና ሰራተኛው ለማህበረሰቡ በአግባቡ አገልግሎት መስጠት እንዳለበትም ተናግረው ተቀናጅተንና ተጋግዘን መስራት አለብን ብለዋል፡፡

ደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ህዳር 11 ቀን 2019 ዓ.ም
November 20, 2026 103 2
ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለማስቀረት ስነ-ምግባር ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ተባለ፡፡… — DebreTabor Communication — TG.ME