ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ከተቃርኖ እና ከጥላቻ ወደ ይቅርታ፣ ስክነት እና መረጋጋት ያሸጋገረ ታሪካዊ ክስተት መሆኑን የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አስታወቁ።
ፕሬዚዳንቱ የምክክር መድረኩ በስኬት መጠናቀቁን አስመልክተው ባስተላለፉት ጠንካራ መልዕክት፤ ሀገራዊ ምክክርን የዘመናዊት ኢትዮጵያ ግንባታ ማዕዘን ለማድረግ የተወሰደው እርምጃ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ደፋር ውሳኔ መሆኑን አብራርተዋል።
ይህ መድረክ ተፎካካሪ ሀሳቦች በስሜታዊነት ሳይሆን በከፍተኛ መከባበር ተንሸራሽረው የተሻለ ሀሳብ የሚወጣበትን ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አጽንዖት ሰጥተውበታል።
ይህን ታሪካዊ የለውጥ ሀሳብ ወደ ተግባር በመቀየር ላሳዩት ጽኑ ቁርጠኝነት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የላቀ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ለሂደቱ ሕጋዊ ማዕቀፍ ላጸደቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንቱ ምስጋና አቅርበዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ ተሳትፈው ለመጪው ትውልድ የሚሻገር ብሩህ ታሪካዊ አሻራ ላኖሩ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችም ጥልቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የምክክር መርሆዎችን በማውጣት እና አጀንዳዎችን በማሰባሰብ ግልጽነት የተላበሰ መድረክ በማዘጋጀት ላከናወነው ስኬታማ ሥራ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ፣ እንዲሁም ይህ ታሪካዊ ውይይት በሰላም እንዲጠናቀቅ ሌሊት እና ቀን ለተጉት የመከላከያ ሠራዊት እና መላው የጸጥታ ኃይሎች ልዩ እውቅና እና ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
#prosperity






