የአባትና ልጅ የታሪክ ቅብብሎሽ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ነሃሴ 17 ቀን 2018 ዓ.ም
ሀገር ያለ ሠው ሠው ያለሀገር ምንም ናቸው። ሀገር ማለት ሠው ነው ሠው ማለትም ሀገር በመሆኑ ሁሉም ሀገሬ ሲል ለሀገሩ ይቆረቆራል፣ ይከፋል፣ መስዋዕት ይከፍላል። የእኛ የኢትዮጵያኖች ሀገር ወዳድነት ደግሞ በብዙ ቱባ ታሪኮች የተሞላ፣ የአብሮነትን የህይወት ኑሮ ያስተሳሰረ ድንቅ ባህል ሆኖ እናገኘዋለን።
በመሆኑም ከአንድ ማህፀን የተፈጠሩ ወንድምና እህቶች፣ አባትን ልጆች፣ ባልና ሚስቶች በተከበረው ወታደራዊ አልባሳት ሀገራቸውን ያገለግላሉ ሥለሀገራቸው መስዋዕት ይሆናሉ። ተከታዩ ታሪክም በአባትና ልጅ ኮማንዶዎች ታሪክ ዙሪያ ያጠነጥናል።
በ1991 ዓ.ም ለሀገሬ ሠላም እዘምታለሁ በሚል እሳቤ በሀገር ፍቅር ስሜት ሀገሩን በውትድርናው ዓለም ለማገልገል ወደ ሠራዊቱ የተቀላቀለው የአሁኑ ሌተናል ኮሎኔል ምትኩ ገብሩ፣ ላለፉት 28 ዓመታት ሀገሩን በታማኝነት በጀግንነትና በጽናት ሲያገለግል ቆይቷል። አሁንም በማገልገል ላይ ይገኛል።
ውትድርና ለሌተናል ኮሎኔል ምትኩ የሙያ ምርጫ ብቻ ሆኖ አልዘለቀም፣ ለትውልድ የሚተላለፍ የክብርና የቃል ኪዳን ውርስ ጭምር እንጂ። በመሆኑም በጀግንነት የጀመረውን የተከበረው የውትድርና ጉዞ የሚያስቀጥል ከአብራኩ የተከፈለው ልጅ እንዲተካው በልቡ ሙሉነት ይመኝ ነበር።
ልጁ ምክትል አሥር አለቃ በረከት ምትኩ ገና ከሕፃንነቱ ጀምሮ የአባቱን የጀግንነት ገድልና የሀገር ፍቅር እየተመለከተ አደገ። በልቡ ውስጥ የተቀጣጠለው ወታደር የመሆን ምኞት በቀላሉ የሚጠፋ አልነበረም። ዕድሜው ባለመድረሱ ምክንያት በተደጋጋሚ ያደረጋቸው ሙከራዎች ባይሳኩለትም ተስፋ ሳይቆርጥ ሕልሙ እውን የሚሆንበትን ቀን በትዕግሥት ጠበቀ።
በ2014 ዓ.ም ምክትል አሥር አለቃ በረከት የአባቱን ፈለግ በመከተል ወደ ሠራዊቱ ተቀላቀለ። ነገር ግን ጉዞው አልጋ በአልጋ አልነበረም። እጅግ ፈታኝ፣ ውስብስብና አካልን የሚያደክመውን የኮማንዶ ስልጠና አልፎ ስኬት ላይ እንዲደርስ አባት ሌተናል ኮሎኔል ምትኩ ከጎኑ አልተለየም። የህይወትን ውጣ ውረድና የሙያውን ክብር የሚያውቀው አባት ልጁን በምክር፣ በመከታተልና በጠንካራ መንፈሳዊ ድጋፍ በማበረታታት ለአሁን የ45ኛ ዙር የኮማንዶ ምረቃ አበቃው።
በምረቃው ዕለት ሌተናል ኮሎኔል ምትኩ በደስታና በኩራት ተሞልቶ ውትድርና የዱላ ቅብብል ነው የእኔ ሀገርን የማገልገል ዘመን እንዳያቆም የአብራኬን ክፋይ ተክቼ የጀግኖችን ሀገር እንዲጠብቅ በመተካቴ እንደ አባት ታላቅ ኩራት ይሰማኛል ሲል ደስታውን ገልጿል።
ምክትል አሥር አለቃ በረከት ምትኩ በበኩሉ፣ ያ በልጅነቱ ይመኘው የነበረው የአባቱ የጀግንነት ፈለግ ዛሬ ፍሬ አፍርቶ ይመኝ የነበረውን ቀዩን መለዬ በመልበሱ፣ ታላቅ ክብር እና ደስታ ተሰምቶታል።
ሀገር በታሪክ ቅብብሎሽ ትቀጥላለች የሚባለውም ለዚሁ ነው። ትላንት በሀገራዊ ጀግንነት ሀገሬን አላስደፍርም ብለው ልዩ ጀብዱ ፈፅመው ያለፋት ጀግኖቻችን ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ መሠረት ጥለው አልፈዋል። እነበረከት ምትኩም ምትክነታቸውን በታሪክ ማህደር አስፍረው ሀገርን ለተተኪ የማስረከቡን አደራ በጀግንነት እንደሚወጡ እሙን ነውና ለመላው የ45ኛ ዙር የኮማንዶና አየር ወለድ ተመራቂዎች መልካሙን ሁሉ ተመኘን።
በልደት አስረስ
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት
https://dfmc.mod.gov.et/
https://youtube.com/@fdredefenseforce-9629?si=Av-sDKCopw1FfTW2
https://t.me/+E_EOiTY9eq85ODI0
https://www.facebook.com/fdredefense.official




















