ዛሬም ሆዳቸው አምላካቸው የሆኑ ጥቂቶች የብላቴናው የእውነት ሰይፍ ገና ከአፎቱ ሳይወጣ የሚርዱት ወደው አይደለም። የሚጠሉት ከሚወዱት በላይ የጥበቡን ጉልበትና ልክ አውቀውታል። ወዶ ገቢውም ሆነ በብር የተሸጠው ሁሉ ከመቅለል የዘለለ እጣ ሳይኖራቸው ቢቅበዘበዙም እውነት ሰፋሪው ህዝብ ግን የነገሰውን ሊያነግስ የቀናት ምጥ ይዞታል።
በአስራዎቹ እድሜያችን የምናውቀው ቴዲ እሱ ወደ ሃምሳ እየገሰገሰ እኛም ወደ አርባ እየቀረብን ነው። እጅግ በጣም የተወደደ። ያለማቋረጥ ያወዛገበ። በገሚስ የተጠላ ፣ ምርቃትና እርግማን የጠገበ... የጠሉት ቢጠሉት እንኳን በዜማው ከመቆዘምም ሆነ በምቱ ከመወዛዘዝ አላመለጡም።
መወደድና ዝና አረቄ ያልሆነበት ብላቴና ከስራው ይልቅ መወደዱን የያዘበት መንገድ ጠቢብነቱን ይመሰክራል። እሱ ወልዶ ከብዶ ቢጎለምስም በመወደድ ብዛት ብላቴናነቱን ሳይለቅ ከፊታችን እየገዘፈ ነው።
ሁሌም በኩራት እንደምለው
ቴዲ ሽበት ነው
በቀለም ልታጠፋው ልትደብቀው ብትሞክር? ከስር በጥበብ በርጋታ ይፈካል! ተደብቆ መጉላት ይችልበታል! በምላጭ ልታጠፋው ስትለፋ ጭራሹን ይበዛል! በጥቁር ሻሽ የማታስረው የሀገር ሽበት! ሳንዘራው ያጨድነው, ያለጊዜው የበቀለ ሽበት! ብቻ አትልፋ ቴዲ ወጣት መሳይ ሽማግሌ ነው ለመጥፋት ስንቃረብ በግጥም መክሮ በዜማ አራርቶ ከልባችን የሚያስታርቀን ወጣት መሳይ ሽማግሌ ነው!
ከፍቅር አስከ ሃገር ልብና አድማሱ ለሰፋለት ፣ አኗኗሩ ምሳሌ ፣ አንደበቱ ፈዋሽ ለሆነለት የዘመናችን መልክ ጥበብና እድሜ ይትረፍለፍለት!
#ኢቶሪካ
✍🏽 ሙሉቃል ቃል
@Bookfor
April 14, 2026 3.1K 3