ሰው በብዙ መልኮች ይለያል!
ሰውን በተለያየ መልኩ ነው የምናየው። የእምነት ተከታይ ሲሆን የሚኖረው ባህሪ አማኝ ሳይሆን ከምናገኘው ፈጽሞ ይለያያል። የብሔሩን እሴትና ትርክት አክባሪ ሆኖም የምናየው ሰው እንዲሁ ሌላ መልክ ይኖረዋል።
ሳይንሳዊ ነኝ ወይም በምክኒያት አምናለሁ ብሎ የተነሳም ሰው ሌላ ነው። ወደ አዋቂነት እድሜ ከተሻገርን በኋላ ነገሮችን ለመረዳት የምንሄድባቸው ስልቶች ከልጅነት እድሜ ይለያል።
ማስተዋልና እውቀትን የግድ እንተዋወቅ ዘንድ የምንገደድበት ዘመንና ገሃድ ውስጥ ነን፥ ስንኖር ነሲባዊ ሆነን የቀናትን ሽግግር እየጠበቁ ማለፍ ከሚያስረሳን ዘመን ውስጥ ነን።
ሰውነትን ማወቅ፤ ራስን መለየት፤ የምንኖርበትን የሕይወት መልክ ተግቶ ማጤንና የሚሻለውን ብይን ተረድቶ መኖር ለውጤትና ስኬታማ ህይወት በኩር ኃይል ነው።
እንደሰው ነጻ ግለሰብ ሆነን እናስብ ይሆናል። እንደኢትዮጵያዊ ሰው ደግሞ ብዙ ኃይማኖቶችና ባህሎች እንዳሉት ሰው የምንሆናቸው ባህሎችና እምነቶች አሉ። ቢያንስ እንደየራሳችን ልዩነት ቢኖረውም የባህሎቹ ተጽዕኖ ግን ጠንካራ ሆኖ እናየዋለን።
ኢትዮጵያዊ ሰው፥ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከመሆኑ በፊት ለኃይማኖቱ ወይም የብሔሩ ስሜት ተዘንባይ ይሆናል። ወይም በታሪካችን የኖርነው ከነዚህ እሴቶች በብዙ ተጣብቀን እንደመሆኑ የሚጠበቅም ነው።
ወደዜጋ ለመሻገር የምክኒያትና ሳይንሳዊነት ባህሎች መፈጠር አለባቸው። በእውቀትና ምክኒያታዊ ሎጂኮች ላይ ጠንካራ መተማመን ያለው ሰው መፈጠር አለበት። ከኃይማኖቱ ትዕዛዝ በፊት አእምሮው የሚሰለጥነው እውቀት ወይም ሳይንስ አቋሙን እንዲመዝንለት ፈቃድ የሚሰጥ ግለሰብ መወለድ ይኖርበታል።
ሀገርና ዜጋ መሆን በቀጥታ ይገናኛሉ። አማኝና እምነት፤ ጎሳና የጎሳ አባል እንዲሁ የሚቆራኙ መሆናቸው እሙን የሆነውን ያህል ማለት ነው።
አንድ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ መባሉን ከማሰቡ ቀድሞ ክርስቲያን መባሉን ይመርጣል። ሙስሊሙም እንዲሁ በተመሳሳይ ሙስሊምነቱን ቅድሚያ ይሰጣል። የጎሳና ብሔሮቻችንን መልክም ከዚህ ብዙ ሳናርቅ ማሰብ ነው።
እምነትና ልማዶች ከትውፊት፥ ትርክትና የመገለጥ ዶክትሪኖች ስለሚወለዱ በርካታ ተከታይን ያፈራሉ። የለማወላቀል እንደወረደ ተቀብሎ የሚተገብር አማኝ ይፈጥራሉ። ባህሎች ይሆናሉ።
ሀገር ግን ከሀሳብና አሳቢያን አተያይ ተመዝና ካልታየች በርካታ ባህሎች በሚኖሩባቸው እንደኢትዮጵያ ያሉ ሀገሮች ሁሉም ጎሳዎችና ሁሉም ኃይማኖቶች ስለሀገር በእኩል አይረዱም። አያስቡም። ሁሉም ከየራሳቸው ባህልና እምነት ተነስተው የሚሰማቸው ይኖራል። ከዛ ተሻግረው እንዲያስቡ ግን ሀሳባዊነት መለምለም አለበት። ግለሰብን የሚሰራው የእውቀት ሳይንሳዊ ባህል መታየት አለበት።
ነብይና ፈላስፋ
👇👇👇
https://tiktok.com/@burhanadisofficial
