ተከብሮ ማርጀትና የዘመኔ ፍፁም መልክ! ፍቅር ጭራሽ አልገባንም። እድሜያችን ለጋ በጣም ለጋ ነበር ! ፊታችን…

ተከብሮ ማርጀትና የዘመኔ ፍፁም መልክ!

ፍቅር ጭራሽ አልገባንም። እድሜያችን ለጋ በጣም ለጋ ነበር ! ፊታችን ፂም አያቅም! እህቶቻችን ጉብ ጉብ አላበቀሉም። በመኖር ብዛት ባልቆሸሸ ልባችን ፈፅሞ ትዝታ በማያቀው እድሜያችን .... የዛሬ 25 አመት አንድ መልከ መልካም ወጣት በማናውቀው አለም ውስጥ በምዕናብ አምነሸነሸን።

የወደድኳት በማለዳ..
በልጅነት በአቡጊዳ...
የፍቅር ቃል መጠሪያዬ...
የመጀመሪያዬ...

እያለ.... እየተስረቀረቀ ሆድ በሚበላ ድምፅ በአዲስ የግጥም አፃፃፍ ፣ ስራ ነገሩ ሁሉ የተለየና ትውልዳችንን ያነሆለለ ግሩም ሰው ተከሰተ።

በዘመነ ካሴት አንድም ዘፈኑ የማይዘለል ዘፋኝ ተገኝቶ የልጅነት አፋችንን አሟሸው። ሳናፈቅር አፈቀርን ፣ የልብ መደላደል ሳይገባን ፣ የስም መጥፋት ህመም ሳያገኘን ያልኖረውን ዘመን ኖርን። ብላቴናው.... "ተረታና ልቤ ለፍቅርሽ ተገዛ
በልቤ ቤት ሰራሽ ሄዋን እንደዋዛ" ን እያቀነቀነ ዛሬም ዘመን ተሻግሮ ያላረጀ ቤቱን በህዝብ ውስጥ ሰርቶ ቁጭ አለ። ወጣትና ህፃናት ጎልማሳና ሽማግሌው አንድ ላይ አበደለት። በየ ቤቱ ፣ ሱቁና ፀጉር ቤቱ ፣ ጫት ቤቱና ካፌው ፣ ታክሲና ባሱ አስፋልቱና መንገዱ አረገዱለት።

ሁሉም ነገር ቀጥ ብሎ ፣ ሁሉም የወሬ ጉልበት ዝሎ ሃገር ጆሮውን ሰጥቶ እየሰማው ተደመመ። 'ልቤ መሸነፉን እንዳይነግራት ሰጋ' ን እያዜመ ልጃገረዶች ሁሉ ተሸነፉለት። ተማሪዎች ከደብተራቸው ጠርዝ ስሙን ፃፉት ፣ ጋዜጦች ተነተኑት! መፅሄቶች የየእትማቸው መልክ አረጉት።

በዘመን ውስጥ ብዙ ሰው ተወዷል ፣ ብዙ ሰው ገኖ ብዙ ሰው ቀሏል። አንድ የ 23 አመት ወጣት በድንገት መጥቶ የሃገሩ ዜማ ሆነ። ተራው ህዝብ ብቻ አይደለም አንጋፎች ሳይቀር ለውዳሴ ተሽቀዳደሙለት።

1993 እንደ ሃገር የነበሩ የፖለቲካ ትኩሳቶች አመፅና ግርግሮች ሳይቀር በብላቴናው አልበም ደበዘዙ። ሃገር ቆም ብሎ አንድ ነገር ሰማ! ስለ አንድ ነገር አወራ።

የመወደዱ ብዛት የፈጠረው የወሬ ግምት ገኖ ገኖ... ቴዲ ከቆነጃጅቶች ጡት ላይ ፈርሟል የሚል ወሬ ሃገሩ ላይ ተዛመተ። ያኔ ልክ እንደዛሬው ጡት በአደባባይ አልዋለም። መሸፋፈን ክብር አለመገለጥ ውበት ነበር። እንደዛሬው ወሬ የሚያዛምት Internet ወለድ የወሬ ማሽን ሳይኖር " እከሌ አበደችለት" "እከሌ በሱ ፍቅር ትዳሯን ፈታች"... የሚሉ አሉባልታዎች አየሩን ሞሉት።

ብላቴናው ሃገር እንደ ጉድ ቢያብደለትም መወደዱ አላሰከረውም። አልበሙን ባወጣ በወራት ጊዜ ውስጥ በወቅቱ በነበረው አንድ ለናቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርቦ ጡት ላይ ስለመፈረሙ ተጠየቀ " ጨዋ ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ ነው ያሳደገኝ" አለ... ሲዘፍን የሰማው ሁሉ አፉን ከፍቶ አይኑን ሰክቶ ሲያወራ ሰማው። አንገቱን የሰበረ አይኖቹ በትህትና የሚንከባለሉ ሆኖ ተገኘ። ሃገር በስስት አየው።

አንጋፋዎቹ ልጄ ልጄ እያሉ ተሻሙበት። አትሌት ሃይሌ ገብረ ስላሴ "እኔ ሩጫ እንጂ ወሬ አልችልበትም" ብሎ ቴዲን ማድነቂያ ቃል አጣ። የዘመኑ አንጋፋዎች እነ ውብሸት ወርቃለማው ቢዘፍንልን ብለው ተመኙ። ቴዲ ከዘመኑ የሚነፃፀር ባለሙያ ታጥቶለት ተንታኞች ከቀደሙት ገናኖች ጋር አወዳደሩት። በብዙዎች ለቴዲ የራሱ አለም ተሰጠው! ብቻውን የሚዳኝ እኩያ የማይገኝለት ሆኖ ማርሽ ቀያሪነት የዜማ ሊቅነት የገጣሚነት ጫፍ ላይ ተቀመጠ!

ገና በ 23 አመቱ መሸከም የሚከብድ ፍቅር ፣ አንገዳግዶ የሚጥልን አድናቆት ቢቀበልም ብላቴናው ከአደባባዮች ጠፍቶ ከግርግሩ እርቆ ከአራት አመታት በኋላ "ያስተሰርያል" በተሰኘ ታሪካዊ አልበም ተከሰተ።

በመጀመሪያ አልበሙ አቡጊዳ እያለ የሃገሬውን ሆድ የበላው ሰው አሁን በአልበሙ ጥግጋት "ብልህ ሰው ታናሹንም ይሰማል" እያለ በትህትና ዝቅ ብሎ ሃገር በጥላቻ እያባከኑ ያሉ ሽማግሌዎችን የሚመክርበትን ግጥምና ዜማ ጠምቆ ሃገሩን እንደ አዲስ አሰከረው! ቴዲ በዚህ አልበም በእያንዳንዱ ስንኝ ውስጥ ተከድኖ የሚነደውን መተንፈሻ ያጣውን የሃገሬውን ህመም ከሰው በማይመስሉ ጌጠኛ ቃላትና ልብ በሚያርዱ ዜማዎች ቀምሞ ሃገሩን አስቆዘመው።

ብላቴናው "ያስተሰርያል" በሚለው አልበሙ ለሃገሩ የቃተተበት ዜማዊ ፀሎት ነው። ፍቅር ማጣታችን የመራባችን ምንጭ መሆኑን ተናገረ። እየዘፈነ ሰበከ ፣ እየወቀሰ መከረ ፣ እየመከረ ምህረት ለመነ። በሚጣሉ ወላጆች መሃል ቆሞ ግራ እንደገባው ህፃን "መለየት አቃተን የሚበጀንን ሰው" እያለ የነፍሱን ጭንቀት አስረዳበት። ግጥሙ ከዜማው ዜማው ከግጥሙ የተዛመዱበትን መንገድ ብዙዎች በእንባ ሰሙት። ቴዲ የብዙዎችን የልብ ህመም እየፈታ የህልማቸውን ሃገር በጥበብ መስኮት ከሰተላቸው።

ኸረ አይነጋም ወይ
አይነጋም ወይ ሌቱ..... ቴዲ ለሃገሩ ቃተተላት

ቴዲ ከመርቀቁ ብዛት እንኳን በሸውራራ አይናቸው የሚያዩት አብዝተው የሚወዱትም በቅጡ የሚረዱት አይደለም። ከጥቂቶች በቀር የሚወዱትም የሚያወራውን ፍቅር አያወሩም። የሚጠሉትም ያለውን በፈለጉት መንገድ ተረጎሙ እንጂ በልቡ ልክ አልሰሙትም!

ያስተሰርያል ፍቅርና አድናቆት ብቻ ሳይሆን የመከራ መስቀል ይዞበት የመጣው ቴዲ የውሸት ክስ ተቀምሞለት በገዢዎች ጉልበት ዘብጥያ ወረደ። ወጣቶች ከፖሊስ ጋር ተፋለሙለት። ቆነነጃጅት ማልደው ከፍርድ ቤት እየተገኙ እናቶች አገልግላቸውን አስረው ተሰለፉለት። በዚህ ሃገር ታሪክ ታስሮ በቅፅበት ያልተረሳ ጉምቱ የለም። ብላቴናው ግን ከክርክር እስከ ፍርድ ከፍርድ እስከ መፈታት ከሰው አፍ ሳይጎድል የመንግስት ራስ ምታት ሆኖ ከወህኒ ቤት ተፈታ።

ወትሮም እንኳን ዘፈኑ ቃለ መጠይቁ የሚናፈቅለት ጥበበኛ 'ከእስሩ በኋላ ምን ይል ይሆን?' በሚል ብዙዎች ጆሯቸውን ቀስረው ቢጠብቁትም ለአመታት እስር የዳረገውን የተከሸነ ክስና በቀል " ፍቅር ግን ሁሉን ያሸንፈል በሚል ከደነው።

ቴዲ እየደመቀ እንጂ እየበሰለ ያልሄደ ተዐምረኛ ሰው ሰው! ሲጀመር ቃላቶቹ የጣፈጡ ሃሳቦቹ የረቀቁ ናቸው። ባሰበት የሚያስብል እንጂ እዚች ጋር ተወነጨፈ የሚያስብል ክፍተት አሳይቶ አያውቅም። በመሃል
ከአልበም በላይ የሚንጡ ነጠላ ዜማዎችን እየለቀቀ ሲለው ተሰርቆና አምልጦ የሚወጣው ስራው ሁሉ የሰው ጆሮ እያጠገበና ልብን እያረሰረሰ ቀጠለ። በዚህ ሁሉ ስኬቱ መሃል ኩራት ከአጠገቡ የለም። ስራው አንግሶት በግርማ ፀጥ ያለ አንበሳን መስሎ ይኖራል። አይንና ጆሮ በበዛበት ልክ "ከአይን ያውጣህ" ብለው የማይመርቁት የረጋ ጥበብ ሆኖ ኖረ።

ከዛ በኋላ የለቀቃቸው ሁለት አልበሞቹ የፈጠሩት ድባብ እንዲህ ነበር ማለት የማይፈታቸው የመፃፍንም ሆነ የማስታወስን ልክ የሚፈታተኑ ሃገራዊ ድባቦች ነበሩ። በተለይም ከጥቁር ሰው በኋላ ያወጣው ኢትዮጵያ የተሰኘው አልበም ሲለቀቅ እያንዳንዱ ቤት ሰርግ ያለ እስኪመስል እያንዳንዱ ገበያና ነጋዴ ሳር ጎዝጉዞ የጠበቀው የአውዳመት ዋዜማ ይመስል ነበር። በጊዜና በቦታው ከነበረ ካየና ካልሰማ በቀር ለታሪክ ነገሪ የማይመች አስደናቂ ድባብ።

ስለ ብላቴናው ብዙ ከመፃፍ ብዙ አይባልም። ብዙ ተፅፎም ጥቂት አይገለፅም! ልባም ሰው ግን ቴዲን እና ስፋቱን በስራዎቹ ውስጥ ዞሮ ለማየት ጆሮዎቹን ከፍቶ በግጥምና ዜማዎቹ ውስጥ ቢውል የበለጠ ይረዳዋል።
April 14, 2026 2.6K 4