ኦርቶዶክሳውያን_ለቅዱሳን_ለምን_ይዘምራሉ? በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ክፍል ፬ (የመጨረሻ ክፍል) የእግዚአብሔርን… — ቤተ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ — TG.ME

#ኦርቶዶክሳውያን_ለቅዱሳን_ለምን_ይዘምራሉ?
በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ክፍል ፬ (የመጨረሻ ክፍል)

የእግዚአብሔርን ክብር አስጠብቃለሁ ብሎ የትርጉም ልዩነቱን ሳይረዳ ለቅዱሳን የሚቀርብን ምስጋና የመተቸት ዝንባሌ ያለው ሰው ግን ይህ አካሔዱ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያጣላው ነው፡፡ ሰሞኑን አንዳንድ ሰዎች ‹የአዳም ፋሲካው ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ› የሚለውን ቃል በመጥቀስ እንዴት ድንግል ማርያም ፋሲካ ትባላለች ‹ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአል› ይል የለምን እንዳሉ ሰማን፡፡ ስለ እንክርዳድ ማውራት እንክርዳድን ዝነኛ እንጂ ስንዴ ስለማያደርገው ተናጋሪዎቹን ትተን ጉዳዩን እናስተውለው፡፡

ወደ ሌላ ዝርዝር ሳንገባ አንድ ጥያቄ እናንሣ ፤ ክርስቶስ ፋሲካ ነው ወይንስ የፋሲካ በግ? ፋሲካ የሚባለው በዓሉ ነው? ወይንስ በጉ ነው? የታረደው በዓሉ ነው? ቢባል ምን ይመለሳል? "ፋሲካን እረድ" ሲል በጉን ነው (2ዜና 35:5)፣ "ይህ ፋሲካ ለእግዚአብሔር ተፈሰከ" ሲል በዓሉን ነው። (2ነገሥ 23:23)

ፋሲካ ሲል በዓሉን ከሆነ መሻገሪያ ፣ ደስታ ማለት ነውና ለድንግል ማርያምም ሊነገር ይችላል፡፡  ‹ታርዶአል› የተባለው ግን በጉን ነውና እመቤታችንን እመ በግዑ (የበጉ እናት) እንጂ የታረደችው በግ ብለናት እንደማናውቅ ግልጥ ነው፡፡ ጨርሶ ለክርስቶስ የተነገረ ቃል ለእርስዋ ለምን ይደገማል? ከሆነ ደግሞ እስቲ የቅዱስ ጳውሎስን ንግግር እንመልከት፡-

ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ 2:20 ላይ ፡- ‹‹ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ›› ብሏል፡፡ አልፎ ተርፎም ‹‹እኔ ለዓለም ከተሰቀልሁበት ከክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ›› ብሏል፡፡ (ገላ. 6፡14)

የዚህ ንግግር ትርጉም ምንድን ነው? ቅዱስ ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ተሰቅሎ ነበር ማለት ነው? የተሰቀለው በቀኙ ነው የግራው?"ለዓለም ተሰቀልኩ" እንዴት አለ? እውን ለዓለም የተሰቀለው ጳውሎስ ነውን? ክርስቶስ አይደለምን? የፋሲካው ሲገርምህ ለዓለም ተሰቅዬአለሁ ያለ መጣ? ጳውሎስ የተሰቀለውን የክርስቶስን ክብር መሸፈኑ ነውን?

እንደዚያ እንዳንል ደግሞ ራሱ ጳውሎስ ‹‹ጳውሎስ ስለ እናንተ ተሰቅሎአልን? እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን›› ብሎ አሳርፎናል፡፡ (1ቆሮ 1፡13) ስለዚህ መተርጎም መብራራት አለበት እንጂ ቃሉ ተመሳሰለ ተብሎ አይብጠለጠልም። ጫማ ይስተካከላል እንጂ እግር አይስተካከልም እንደሚባለው መስተካከል ያለበት የእኛ አረዳድ እንጂ የመጽሐፉ ቃል አይደለም።

ሐዋርያው ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ ሲል  የክርስቶስን የመከራ መንገድ ተከትያለሁ ፣ የመከራው ተሳታፊ በመሆን የክብሩ ተካፋይ እሆናለሁ ሲል ነው። "ለዓለም ተሰቅልኩ" ያለው ደግሞ በክርስቶስ መከራ በማመኔ ለዓለማዊ የኃጢአት ሥራ ሙት ሆኜአለሁ ማለቱ ነው ብለን እናብራራለን እንጂ ጳውሎስ የጌታን ክብር ተጋፋ አንልም፡፡

ቅዱሳንን የምናመሰግናቸው የእግዚአብሔር ስለሆኑና ነቢዩ እንዳለው "እግዚአብሔርም በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ስለሆነ ነው" ሥዕሉ ሲደነቅለት የሚበሳጭ ሠዓሊ እንደሌለ ሁሉ የእርሱ ድንቅ ሥራዎች ሆነው ፣ እርሱን አገልግለው ሲወደሱ ፈጣሪን ደስ ይለዋል እንጂ አያዝንም። ጠርሙስ ሰብራ ሽቱን በእግሩ ላይ ላፈሰሰለች ሴት "ወንጌል በሚነገርበት ሥፍራ ሁሉ ያደረገችው ነገር ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል" ብሎ የተናገረ ጌታ አንገታቸው ተሰብሮ ደማቸውን ስለ ስሙ ስላፈሰሱ ቅዱሳን በዓለም ሁሉ ቢነገርና ቢዘመር የሚከለክል አይደለም። (ማቴ 26፥13)

ምስጋና እንኳን ለቅዱሳን በሃይማኖታችን ከጸናን ለእኛም ለደካሞቹም አልተከለከልንም  ፣  እንዲህ ተብሎ ተጽፎአልና :–

"ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፥ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፥ ምስጋናም ይብዛላችሁ" ቆላስ 2፥7
❤49🙏8
September 2, 2026 2.6K 30