አንዳንዱ አይሆንም ብለን የጣልነውን፤ አልፈልገውም ብለን የገፋነውን ተንከባክቦ ያስወድደዋል። አንዳንዱ ፀልየን ያጣነውን፤ ሽተን ያልተቸረንን አግኝቶ ያራክሰዎል።
የሶሊያና ሰርግ ላይ ተገኝቼ ድብርት እየናጠኝ ነው።
የደበረኝ ቀኑ ዱካካም ስለሆነ ነው!! የደበረኝ እሁድ ስለሆነ ነው!! ትራፊክ ፖሊስ አርብ ለ'ታ ስለቀጣኝ ነው!!
የደበረኝ ስለደበረኝ ነው...
ግን...
ሶልያና እንዲህ ደርባባ ነበረች !?
ስትስቅ እንዲህ ደስ ትላለች !?
የፊቷ ቀለም እንዲህ ያምራል !?
ሶልያናን ምኗን ነበር ያልወደድኩት??
እኔንጃ!!
ሶልያና አማራጭ እንዳላት አላውቅም ነበር?
መውደዷ ስስት አልነበረውም፤ ሙላቴ ላይ ነው የምታተኩረው፤ ችስታነቴ አሳስቧትም፥ አሳታውሰኛም አታውቅም።
ሶልያና አሪፍ ነበረች !!
ፍቅሯ ጥበብ ስላልነበረው ነው !?
በጣም ስለፈለገቺኝ የምታንሰኝ መስሎኝ ነው!?
ትዳር ስለምፈራ ነው !?
ዝምብ'ሎ ስለሆንኩኝ ነው!?
ለምን ሶልያናን እኔ አላገባኋትም?
ለምን የኔ እንድትሆን ልቤ ተመቀኘ?
አእምሮዬ ምን አባቱ ሆኖ ነው ይቺ ሶልያና ያቺ ሶልያና እንደሆነች ያልገለፀልኝ??
ካልተከለከልኩ ውድነትን፥ ውበትን መመልከት አልችል ይሆን??
'ልጅ እያለሁ አማኑ ዛሬን ብቻ ነው የሚያየው' ይል ነበር አባቴ። አባቴ ስለሆነ አዝኖልኝ ነው እንጂ ዛሬንም በደንብ ማየት አልችልም።
ዛሬን በደንብ ያ'የ ነገ ይታየዋል ኣ !!
የአሸነፍነው በመሰለን ውጤት ላይ መውደቅ ደስስ አይልም !!
ሶልያናን ስታገባ ጠብቄ ወደድኳት።
ባሏ ሲያስጠላ፥ እሷ ስታስጠላ፥ እድምተኛው ሲያሽቃብጥ ሲያስጠላ ...
ቀስ ብዬ ከስርግ አዳራሹ ወጣሁ.....አወጣጤ እና ሁኔታዬ ከለቅሶ ቤት ይመስል ነበር ...
በርግጥ .....ሰፍራ ብቻውን ውጤት አይቀይርም!!
© Adhanom Mitiku




