ሩሲያ በዴንማርክ መከላከያ ኢንዱስትሪ ላይ የማጥፋት ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጀች መሆኗን የዴንማርክ የመረጃ ተቋም አስታወቀ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም (#አዲስ_ማለዳ)
የሩሲያ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎቶች በዴንማርክ የመከላከያ ኢንዱስትሪ ላይ የማጥፋት እና የማውደም ድርጊቶችን ለማካሄድ በንቃት እየተዘጋጁ መሆኑን የዴንማርክ የደህንነትና የመረጃ አገልግሎት ገልጿል ።
አናዶሉ የዴንማርክ የሕዝብ ሚዲያ መረጃን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የሩሲያ የመረጃ አገልግሎቶች ከዩክሬን ጋር በተያያዙ የመከላከያ ድጋፎች ጋር የዴንማርክ ኩባንያዎች ላይ ሊያካሂዱ የሚችሉትን የማጥፋት ድርጊት እያቀዱ ነው ብሏል ።
የፀረ-መረጃ ሥራ ኃላፊ ኤሚል ግሬስሆልም እንደገለፁት ከሆነ የዴንማርክ ኩባንያዎችም ለተወሰኑ የሩሲያ የጥፋት ዕቅዶች ዒላማ እየሆኑ መሆኑን ጠቁመዋል ። አከውም የሩሲያ የመረጃ አገልግሎቶችም በዴንማርክ የመከላከያ ኢንዱስትሪን ዒላማ ያደረጉ የማጥፋት ድርጊቶችን ለመፈጸም በንቃት እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።
ግሬስሆልም ለዴንማርክ ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በዴንማርክ በሚገኙ ኩባንያዎች ላይ ከባድ ጥፋት ለመፈፀም የተዘጋጁ የሩሲያ ዕቅዶችን ለይተው እንዳገኙ በመግለጽ “ይህ አንድ ቀን ወደ ዴንማርክ ሊደርስ የሚችል ስጋት ብቻ አይደለም፣ ዕቅዱ አሁን እየተዘጋጀ መሆኑን በተጨባጭ እያየን ነው” በማለት ተናግረዋል ።
በተጨማሪም የመረጃ ተቋሙ እንዳለው ከሆነ ሩሲያ በማኅበራዊ ሚዲያና ሌሎች የኦንላይን መድረኮችን በመጠቀም ተራ የዴንማርክ ዜጎችን ለመመልመል እየሞከረች እንደሆነ እና ይህም ተጨባጭ መረጃ እንደሆነ ለይቻለሁ ብሏል ።
እነዚህ ሰዎች የማጥፋት ድርጊት ዕቅድ ለማውጣት እንዲያግዝ የኩባንያዎችን ወይም የተቋማትን ፎቶ እንዲያነሱ ያሉ ሥራዎችን ሊሰጣቸው እንደሚችል ተቋሙ ገልጿል።
ግሬስሆልም፣ “ተራ የዴንማርክ ዜጎች ሆን ብለውም ሆነ ሳያውቁ ለሩሲያ የመረጃ አገልግሎቶች እገዛ እንዳያደርጉ አፅንኦት ሰጥተው አሳስበዋል ።
የመርጃ ተቋሙ ከዴንማርክ የመከላከያ መረጃ አገልግሎት እና ከዴንማርክ የማኅበራዊ ዋስትናና ዝግጁነት ኤጀንሲ ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ገልጿል።
ተቋሙ በተጨማሪም ስለስጋቱ ያለውን ግምገማ ለፖሊስ ክልሎች በየጊዜው እንደሚያሳውቅ የገለፀ ሲሆን
ግሬስሆልም እንደገለጹት፣ ባለሥልጣናት ለተመረጡ ኩባንያዎችና የኢንዱስትሪ ድርጅቶች ስለስጋቱ በተደጋጋሚ መረጃ ሰጥተዋል፤ ከሌሎች ተቋማት ጋርም በመተባበር የተለያዩ የደህንነት እርምጃዎችን መክረዋል።
የመከላከያ ኢንዱስትሪውም ራሱን ለመጠበቅ “አስፈላጊውን የደህንነት እርምጃ” መውሰድ እንዳለበት ግሬስሆልም አሳስበዋል። ይህ ስጋትም ለህዝብ ይፍ እየተደረገ መሄዱን ተወድሷል።
የዴንማርክ ኢንዱስትሪ ማኅበር በበኩሉ የመረጃ ተቋሙን ግምገማ በቁም ነገር እንደሚወስድና ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ገልጿል። የኢንዱስትሪ ማህበሩም ሆነ የሀገሪቱ ባለስልጣናት መጣ የተባለውን ስጋት ለመቋቋም የበለጠ ትክርት እንደሚሻ በማንሳት በመረጋጋት ተመጣጣኝ እርምጃ ያስፈልጋል ብለዋል። በተጨማሪም የደህንነት እና የአደጋ ጊዜ ስርዓቶች ዝግጁነት በትክክል እየሰሩ መሆኑን መፈተሽ እንዳለበት አስጠንቅቀዋል።
የዴንማርክ ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ፍሌሚንግ ስፕሊ ድስቦል በብኩሉ የተቋሙን ማስጠንቀቂያ “አሳሳቢ” በማለት ገልጸው ስጋቱ “አዲስ፣ ተጨባጭ እና የተራቀቀ” መሆኑን ተናግረዋል።
የቀድሞው የዴንማርክ የመከላከያ መረጃ አገልግሎት ዋና ተንታኝ ያኮብ ካርስቦ በበኩላቸው የመርጃ ተቋሙ ጉዳዩን በይፋ ለማሳወቅ መወሰኑ የዴንማርክ ባለሥልጣናት የሩሲያን እንቅስቃሴ እንደሚያውቁ ለሩሲያ ለማሳየት የታለመ ሊሆን እንደሚችል መግለፁን ተዘግቧል።
ተጨማሪ ዜናዎችንና አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት የማሕበራዊ ሚዲያ ገጾቻችን ይጎብኙ፦
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
Twitter ➲ t.ly/mxA
Telegram
Addis Maleda - አዲስ ማለዳ
ዜና ከምንጩ

5
1September 3, 2026 3.2K 2